በኒውዝላንድ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተከለከሉ ስሞች
ሀገሪቱ እንደ “ንጉስ”፣ “ቅዱስ”፣ “ልኡል”፣ “ፍትህ” እና “ጌታ” ያሉ ስሞችን ለልጆች መስጠትን ከልክላለች
ስሞች የጠሪውን ህዝብ ክብር የሚጋፉ እና ህግን የሚጻረሩ እንዳይሆኑ በሚል ሀገራት ክልከላ ያወጣሉ
በደቡብ ምዕራብ ፓስፊክ ውቅያኖስ የምትገኘው ደሴት ሀገር ኒውዝላንድ ወላጆች ለልጆቻቸው እንዳያወጧቸው ያለቻቸውን ስሞች ይፋ አድርጋለች።
የሀገሪቱ የዜግነት ጉዳዮች መስሪያ ቤት በ2023 ለልጆች መውጣት የለባቸውም ብሎ ከዘረዘራቸው ስሞች “ንጉስ ወይም ንግስት”፣ “ቅዱስ ወይም ቅድስት”፣ “ልኡል ወይም ልዕልት”፣ “ጌታ”፣ “ፍትህ” እና “ጀነራል” የሚሉት ይገኙበታል።
እነዚህ ስሞች በሌሎች ሰዎች ላይ ያልተገባ ጫናን እንዳይፈጥሩ አልያም እንዳያሸማቅቁ በሚል ነው የታገዱት።
በዊሊንግተን እንደ “ፍትህ” እና “ንጉስ” ያሉ ስሞች በተለይ ከፈረንጆቹ 2001 ወዲህ በስፋት እንደሚወጡ የሩስያን ታይምስ ዘገባ ያመላክታል።
በጣም ረጅም እና ማዕረግን የሚያመላክቱ ስሞችም በሀገሪቱ የዜጎች የልደት፣ ሞትና ጋብቻ ተከታታይ ቢሮ ተቀባይነት የላቸውም።
የቢሮው ዳይሬክተር ጄፍ ሞንትጎምሪ እንደሚሉት፥ ወላጆች ለልጆቻቸው ስሞችን ሲያወጡ ለራሳቸው ከሚሰጣቸው ትርጉም ባሻገር በሌሎች ሰዎች ዘንድ የሚኖረውን ተቀባይነትን ሊያስቡበት ይገባል።
ኒውዝላንድ የስም አወጣጥ መመሪያን ካወጣች በኋላ በወንዶች “ኦሊቨር” በሴቶች ደግሞ “ኢስላ” የሚሉት ስሞች በርከት ብለው ወጥተዋል።
ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያወጧቸው የማይገቡ ስሞችን ይፋ በማድረግ ኒውዝላንድ የመጀመሪያዋ አይደለችም።
በሳኡዲ አረቢያ እንደ “ሙሃመድ ሳሌህ” ያሉ ቅይጥ ስሞች እና የእስልምና ህጉን የሚጻረሩ (“አብዱል ረሱል”) ስሞች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በአዋጅ ደንግጋለች።
በግብጽም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ የመጡና ትርጉም አልባ ናቸው የተባሉ እንደ “ላራ”፣ “ያራ”፣ “ራማ”፣ “ማያ”፣ “ሬናድ” እና “ሬማስ” ያሉ ስሞችን ማውጣት የሚከለክል ህግ ባለፈው አመት ለፓርላማው ቀርቦ እንደነበር አል አረቢያ አስታውሷል።