የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ለስራ ጉብኝት ወደ አረብ ኢምሬትስ አቀኑ
ፕሬዝዳንቱ ወደ አቡዳቢ ያቀኑት በፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ይፋዊ ግብዣ መሰረት ነው ተብሏል
ፕሬዝዳንቱ ከጉብኝታቸው አስኪመለሱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሳዲያ ሳማታር በተጠባባቂ ፕሬዝዳንተነት ሀገሪቱን ሲመሩ ይቆያሉ ተብሏል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ለይፋዊ ስራ ጉብኝት ወደ አረብ ኢምሬትስ አቅንተዋል፡፡
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት (ቪላ ሶማሊያ) በትዊተር ገጹ ባጋራው ጽሁፍ ፤ ፕሬዝዳንቱ ወደ አቡዳቢ ያቀኑት የአረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ባደረጉላቸው ይፋዊ ግብዣ መሰረት ነው ብሏል፡፡
የጉብኝቱ ዋና ዓላማ “የሁለቱን ወንድማማች ሀገራት ግንኙነት ለማሻሻል እና ለማጠናከር” እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
በቅርቡ የሶማሊያ ፕሬዝዳንትነት በትረ ስልጣን የተቆጣጠሩት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ “ሰላም የሰፈነባት እና ከዓለም ጋር ሰላም ያላት ሀገር ለማድረግ እሰራለሁ” ሲሉ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም፡፡
ለዚህም ፕሬዝዳንቱ ፤ ሶማሊያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር መልካም የሚባል ወዳጅነትና ዝምድና እንዲኖራት በዲፕሎማሲው መስክ በርካታ ስራዎች መስራት እንደሚጠበቅባቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የአሁኑ የፕርዝዳንቱ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጉቡኝትም የዚሁ አንድ አካል ነው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ፕሬዝዳንቱ አቡዳቢ ጉብኝታቸው አጠናቀው አስኪመለሱ ሀገሪቱ ፓርላማ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሳዲያ ሳማታር በተጠባባቂ ፕሬዝዳንተነት ሀገሪቱን ሲመሩ ይቆያሉ ተብሏል፡፡
ሳዲያ ሳማታር፤ በተጠባባቂ ፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ዋና አፈጉባኤው ስለሌሉ መሆኑም ታውቋል፡፡
አጋጣሚው ሰማሊያ በተጠባባቂነትም ቢሆን በሴት ፕሬዝዳንት እንደትመራ እድል የፈጠረ መሆኑም ነው እየተገለጸ ያለው፡፡