የሙሉ ጊዜ ስራውን ከአስተናጋጀነት ወደ “ኔይማርን መምሰልነት” የለወጠው ብራዚላዊ
የኳታር ድምቀት ሆነው ከሰነበቱት ሰዎች መካከል የኔይማር መንታ ወንድም የሚመስለው ወጣት አንዱ ነው
በማህበራዊ ሚዲያዎች ከ1 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን ያፈራው ኢገን ኦሊቬራ ኔይማርን መምሰሉ እንጀራ ሆኖለታል
በቅርቡ 8 ቢሊየን ከደረሰው የአለም ህዝብ አንድ ሰባተኛው በመልክ የመመሳሰል እድል እንዳለው ይነገራል።
22ኛውን የአለም ዋንጫ እያስተናገደች ባለችው ኳታርም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ክስተት ታይቷል። መልክና ቁመናው ቁርጥ ኔይማርን የሚመስለው ኢገን ኦሊቬራ የዶሃ ተጨማሪ ድምቀት ሆኖ ሰንብቷል።
አለባበሱ፣ የጺምና ጸጉር ቁርጡም ሆነ ንቅሳቱ ከፓሪስ ሴንት ጀርሜኑ ተጫዋች ጋር አንድ አይነት ነው።
የብራዚል ብሄራዊ ቡድንን የመለማመጃ ልብስ ለብሶ ሲንቀሳቀስ የተመለከቱ የዶሃ ስታዲየሞች ጠባቂዎች ሳይቀሩ ኔይማር መስሏቸው ነበር።
በስታዲየም የተገኙ ተመልካቾችም ከኔይማር አምሳያ ጋር ፎቶ ሲንሱ የሚያሳይ ምስል በቴሌቪዥን ስክሪን ሲታይ “ጉዳት ላይ የነበረው ኔይማር ከደጋፊዎች ጋር ኳስ እየተመለከተ ነው” የሚሉ ዘገባዎች እስከመውጣት ደርሰዋል።
ኦሊቬራ መልኩ ብቻ አይደለም ከኔይማር ጋር የሚመሳሰለው። በአጃቢዎች መንቀሳቀሱም ትክክለኛውን ኔይማር እንዲመስል አግዞታል።
በዶሃ ወደ አንድ የጫማ መደብር ሲያመራም የብራዚሉ ኮከብ መስሏቸው በርካታ ስዎች አካባቢውን በማጨናነቃቸው ሱቁን ለተወሰነ ጊዜ መዝጋት ግድ ብሎ እንደነበር አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
አለም ዋንጫው የዝና ካባ ከደረበላቸው ኬንያዊው የባቡር ጠቋሚ እና “ሜሲ የታለ?” ከሚለው የሳኡዲ ዜጋ የሚመደበው ኦሊቬራ፥
አሁን ላይ የኢንስታግራም ተከታዮቹ ቁጥር 1 ሚሊየንን ተሻግሯል፤ በቲክቶክም የሚለቃቸው ምስሎች ሚሊየኖች ጋር እየደረሱ ነው።
በብራዚል በአስተናጋጅነት ይተዳደር የነበረው ኦሊቬራ ኔይማርን ትመስላለህ የሚሉትን ደንበኞቹን መመረቅ ጀምሯል።
አሁን የሙሉ ጊዜ ስራው ከአስተናጋጅነት ወደ ኔይማርን መምሰልነት መለወጡንም ነው የሚናገረው።
“ይህ ሁሉ ይመጣል ብዬ አስቤው አላውቅም፤ በርካታ ሀገራትን ጎብኝቻለሁ፤ ጉምቱ ስዎችንም ያገኘሁባቸው የማይገኙ እድሎች ገጥመውኛል፤ ኔይማር ህይወቴን ቀይሮታል” ይላል አምሳያው ኢገን ኦሊቬራ።
ወደ ሀገሩ የተመለሰው “የኔይማር መንትያ’’ ብራዚል ለአለም ዋንጫው ፍጻሜ ከደረሰች ወደ ዶሃ እመለሳለው ብሏል።