የፈረንሳዩ ፒ.ኤስ.ጂ ምባፔ፣ ኔይማር እና ማርኮ ቬራቲን ከስብስቡ ውጪ አደረገ
ፒ.ኤስ.ጂ ዛሬ ምሽት የፈረንሳይ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሎሪየንት ጋር ያደርጋል
አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ “በአንዳንድ ተጫዋቾች ላይ የምወስነው ውሳኔ ግልጽ በሆነ መንገድ ይታያል” ብለዋል
የፈረንሳዩ የእግር ኳስ ክለብ ፒ.ኤስ.ጂ ሶስት ትላልቅ ተጫዋቾቹን ከቡድን ስብስብ ውጪ ማድረጉን አስታውቋል።
ፒ.ኤስ.ጂ ከዝውውር እንዲሁም ካለመግባባት ጋር በተያያዘ ኮከብ ተጫዋቾቹን ዛሬ ከሚያደርገው ጨዋታ ቡድን ስብስብ ውጪ ማድረጉን ክለቡ አስታውቋል።
የፈረንሳይ ሊግ ዋን ጨዋታ ዛሬ የሚጀመር ሲሆን፤ ፒኤስጂ ዛሬ ምሽት የፈረንሳይ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሎሪየንት ጋር እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
በዚህ ጨዋታ ላይ በሚሳተፈው ቡድን ስብስብ ውስጥም ፈረንሳዊውን የፊት መስመር ተጨዋች ኪሊያን ምባፔ፣ ብራዚላዊው ኮከብ ኔይማረ ጁኒየር እና ማርኮ ቬራቲ እንዳልተካተቱ ክለቡ አስታውቋል።
ውሳኔውን አስመልክቶ የፒ.ኤስ.ጂ አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ “ የምንወስዳቸውን እርምጃዎችን ታያላችሁ፣ በተሰወኑ ተጫዋቾቻችን ላይ የወሰድናቸው ውሳኔዎች በግልጽ የሚታዩ ናቸው” ብለዋል።
ፈረንሳዊውን የፊት መስመር ተጨዋች ኪሊያን ምባፔ ውል ከማደስ ጋር በተያያዘ ከፒ.ኤስ.ጂ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ የገባ ሲሆን፤ ከሳዑዲቀው ክለብ የቀረበለተን የ1 ቢሊየን የዝውውር ሂሳብ ውድቅ ማድረጉም ይታወሳል።
ብራዚላዊው ኮከብ ኔይማርም በፒ.ኤስ.ጂ መቆየት እንደማይፈልግ ማሳወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ወደ ቀድሞ ክለቡ ባርሴሎና ለመመለስ ቅድመ ሁኔታ መጀመሩ ታውቋል።
በተጨማሪም ኔይማር ወደ አሜሪካ አሊያም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሊያመራ ይችላል የሚሉ መረጃዎችም ከሰሞኑ ሰወጡ ነበር።
ማርኮ ቫሬቲም ከሳዑዲ አረቢያ ክለብ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱ ነው እየተነገረ ያለው።
በተያያዘ ዜና የባርሴሎናው የቀድሞ ተጫዋች ፈረንሳያዊው ኦስማን ዴምቤሌ የፈረንሳዩ የእግር ኳስ ክለብ ፒ.ኤስ.ጂን መቀላቀሉ ታውቋል።
ዴምቤሌ በ50.4 ሚሊየን ዩሮ ክፍያ ፒ.ኤስ.ጂን የተቀላቀለ ሲሆን፤ ለ5 ዓመት የሚቆይ ኮንትራትም ከፒ.ኤስ ጂ ጋር ተፈራርሟል።