የሳኡዲ አረቢያው አል ሂላልም ተጫዋቹን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ከጀመረ ሰነባብቷል
ብራዚላዊው አጥቂ ኔይማር ጁኒየር ሊዮኔል ሜሲን ተከትሎ ወደ አሜሪካ ሊያቀና እንደሚችል ተነገረ።
ጣሊያናዊው ታዋቂ የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ እንደገለጸው፥ የአሜሪካው ሎስ አንጀለስ የእግርኳስ ቡድን ኔይማርን ለማስፈረም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።
የአሜሪካ ክለቦች ተጫዋቹን ለማስፈረም ፍላጎት ቢኖራቸውም ኔይማር ቅድሚያ የሚሰጠው ወደ ባርሴሎና መመለስን ነው ይላል ፋብሪዚዮ ሮማኖ።
የፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ግን ተጫዋቹን በርካሽ ዋጋ ማዛወር እንደማይፈልግና ለዝውውሩ እስከ 165 ሚሊየን ዶላር እንደሚጠይቅም በማንሳት።
የ31 አመቱ አጥቂ ወደ አሜሪካ ካመራ ከቀድሞ የክለብ አጋሩ ሊዮኔል ሜሲ ጋር በሜጀር ሊግ ሶከር ዳግም ይገናኛሉ።
ፒኤስጂ እየጠየቀው ያለውን 165 ሚሊየን ዶላር የዝውውር ወጪ ባርሴሎናም ሆነ ሎስ አንጀለስ ኤፍሲ ይከፍላሉ ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።
በዚህም በርካታ ተጫዋቾችን በዚህ የክረምት የዝውውር መስኮት ያስፈረሙት የሳኡዲ ክለቦች በኔይማር ላይ አይናቸውን ስለመጣላቸው ጎል ስፖርት ዘግቧል።
የሳኡዲው አል ሂላል በተለይ ኔይማርን ለማስፈረም ጥረት እያደረገ ነው ተብሏል።
ተጫዋቹን አስፈርሞ ለባርሴሎና በውሰት ለመስጠትና ደመወዙን በሶስት አማራጮች ለመክፈል መታሰቡም በትናንትናው እለት በወጡ ዘገባዎች ተመላክቷል።