ኔታንያሁ የጦር ካቢኔያቸውን መበተናቸውን ባለስልጣናቱ ተናገሩ
ኔታንያሁ ካቢኔውን የበተኑት የመሀል ፓለቲካ አራማጁ የቀድሞ ጀነራል ቤኒ ጋንዝ ከካቢነው መውጣታቸው ተከትሎ ነው
ስምንት ወራትን ያስቆጠረው የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ወደ ተኩስ አቁም እንዲያመራ የተጀመረው አለምአቀፍ ጥረት እስካሁን አልተሳካም
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ስድሰት አባላት ያሉትን የጦር ካቢኔ በመተናቸውን የእስራኤል ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ኔታንያሁ ካቢኔውን የበተኑት የመሀል ፓለቲካ አራማጁ የቀድሞ ጀነራል ቤኒ ጋንዝ ከካቢነው መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
ኔታንያሁ አሁን ላይ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአብ ጋላንት እና በካቢኔው ውስጥ የነበሩት የስትራቴጂክ ጉዳይ ሚኒስትር ሮን ደርመር ካሉበት የሚኒስትሮች ቡድን ጋር ስለጋዛው ጦርነት እንደሚመካከሩ ተገልጿል።
የፋይናንስ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች፣ የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን ጊቪር እንዲሁም ብሔርተኛ እና ሀይማኖታዊ የሆኑት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አጋሮች በጦር ካቢኔ ውስጥ ለመካተት ጥያቅ እያቀረቡ ናቸው። የጦር ካቢኔው የተቋቋመው ባለፈው ጥቅምት ወር የጋዛው ጦርነት ሲጀመር ተቃዋሚው ቤን ጋንዝ በሀገራዊ ጥምር መንግስት ውስጥ ከኔታንያሁ ጋር አብረው ለመስራት ከተስማሙ በኋላ ነበር።
ጋንዝ ከጥምር መንግስቱ የወጡት ኔታንያሁ ለጋዛ ጦርነት ስትራቴጂ መንደፍ አልቻሉም የሚል ምክንያት በመስጠት ነው።
ስምንት ወራትን ያስቆጠረው የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ወደ ተኩስ አቁም እንዲያመራ የተጀመረው አለምአቀፍ ጥረት እስካሁን አልተሳካም።
በቅርቡ አሜሪካ ያቀረበችውን ባለሶስት ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እቅድ እስራኤል ከነክፍተቱ እንደምትቀበለው ብትገልጽም፣ ሀማስ ግን አልተቀበለውም።
ሃማስን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ ያለመችው እስራኤል በግብጽ ድንበር የምትገኘውን የራፋ ከተማ ማጥቃቷን ቀጥላለች።
እስራኤል በራፋ እያካሄደችው ባለው ጦርነት ስምንት ወታደሮቿ በትናንትናው እለት በተፈጠረ ፍንዳታ መገደላቸውን ጦሩ አስታውቋል።
የወታደሮች ሞት ጋንዝ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ያጋጠማቸውን የፓለቲካ ቀውስ ያባብሳል ተብሏል።
ሀማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፍቶ 153 ሰዎች ካገተ እና 1200 የሚሆኑትን ከገደለ በኋላ እስራኤል እየወሰደች ባለው የአጸፋ እርምጃ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ37ሺ ማለፉን የጋዛ ጤና ባለስልጣናት ይገልጻሉ።