እስራኤል የኳታሩን አልጄዚራ ቴሌቪዥን እንደምታግድ ኔታንያሁ ተናገሩ
እስራኤል አልጀዚራ ከአረብ ሀገራት ጋር እያጣላኝ ነው የሚል ክስ ቀደም ሲል አቅርባለች
ኔታንያሁ በቅርቡ ፓርላማው ተሰብስቦ እግዱን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ህግ ያወጣል ብለዋል
እስራኤል የኳታሩን አልጄዚራ ቴሌቪዥን በሀገሪቱ እንዳይታይ እንደምታደርግ ኔታንያሁ ተናገሩ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአልጀዚራ ቴሌቪዥን በእስራአል እንዳይታይ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን በቃል አቀባያቸው በኩል ተናግረዋል።
ኔታንያሁ በቅርቡ ፓርላማው ተሰብስቦ እግዱን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ህግ ያወጣል ብለዋል።
የልኩድ ፓርቲ መግለጫ እንደገለጸው ፓርላማው እቅዱን ካጸደቀው በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በህግ በተቀመጠው አሰራር መሰረት የአልጀዚራ ስርጭት በእስራኤል እንዲቋረጥ አስቸኳይ እርምጃ ይወስዳሉ።
እሰራኤል አልጀዚራ ከአረብ ሀገራት ጋር እያጣላኝ ነው የሚል ክስ ቀደም ሲል አቅርባለች።
በዚህ ጉዳይ በእስራኤል ያለው የአልጀዚራ ቢሮም ይሁን በዶሃ ያለው የኳታር መንግስት ያለው ነገር አለመኖሩን ሮይተርስ ዘግቧል።
አልጀዚራ ከዚህ በፊት እስራኤል ስልታዊ በሆነ መንገድ በቢሮው እና በሰራተኞቹ ላይ ጥቃት እየሰነዘረችብኝ ነው የሚል ክስ አቅርቦ ነበር።
እስራኤል ከዚህ በፊት በአልጀዚራ ዘገባዎች ላይ ቅሬታ ስታቀርብ የነበረ ቢሆንም የኳታርን የአደራዳሪነት ሚና ከግምት በማስገባት እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥባለች።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤልን ድንበር ጥሶ እግታ እና ግድያ ከፈጸመ ወዲህ ዶሃ ባደረገችው ድርድር እስራእል የተወሰኑ ታጋቾችን ማስለቀቅ ችላለች።
ነገርግን ሁለተኛው የተኩስ አቁም ድርድር የትም የሚደረስ አይመስልም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ባለፈው ጥር ወር ኳታር በሀማስ ላይ ጫና እንድታሳድር ጥሪ አቅርበው ነበር። ኳታር የሀማስ የፓለቲካ ቢሮ እና ከፍተኛ አመራሮች መቀመጫ ነች። በአልጀዚራ ላይ የተፈጸመው ዛቻ የዚህ ጫና አካል እንደሆነ የተጠየቁት የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ አቪ ሀይማን ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ ባይሰጡም "ጣቢያው ለብዙ አመታት ፕሮፓጋንዳ እየረጨ ነው" ብለዋል።
ብዙዎች አልጀዚራ በህግ ከመዘጋት የሚድንበት አግባብ አለ ቢሉም፣ ሀይመን "ያ የህግ ጉዳይ ነው፤ እኛ ገና እዚያ አልደረስንም" ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
የእስራኤል የኮሙኒኬሽን ሚኒሰትር አልጀዚራን ለሀማስ የወገነ መረጃ በማስተላለፍ እና የእስራኤልን ወታደሮች ለደፈጣ ጥቃት በማጋለጥ ባለፈው ጥር ወር መክሰሳቸው ይታወሳል። በዚህ ጉዳይ የኳታር መንግስትም ሆነ አልጀዚራ መልስ አልሰጡም።
ይህን ክስ ተከትሎ እስራኤል አልጀዚራን በመተው ውስን ተደራሽነት ባለው የሊባኖሱ አል ማየዳን ቻናል ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ትዕዛዝ ማስተላለፏ ይታወሳል።
በአልጀዚራ ላይ እግድ ለመጣል የወጣው ረቂቅ ህግ በቀጣይ ሰኞ በክንሴት(ፓርላማ) ይቀርባል።
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ባለው መጠነሰፊ የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት እስካሁን ከ32ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የፍልስጤም የጤና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።