ኒጀር ከሩዋንዳ ዘር ፍጅት ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸውን ሩዋንዳውያንን አባረረች
እነዚህን ዜጎች ኒጀር ከተመድ ተቀብላ ስታስተናግዳቸው ነበር
ኒጀር አስጠግታቸው የነበሩትንና ከሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸውን ሩዋንዳውያን ማበረሯን አስታወቀች
ኒጀር በ1994 ዓ.ም በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ ከተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸውን ሩዋንዳውያን ማባረሯን አስታወቀች፡፡
ከኒጀር እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ስምንት ሩዋንዳውያን ከአንድ ወር በፊት ወደ ኒያሚ ሲመጡ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር፡፡ እነዚህ ሩዋዳውያን ከኒጀር ግዛት እንዲወጡ ትዕዛዙ የላለፈው በሚኒስትሮች ደረጃ ነው ሲል ሲጂቲኤን ኤኤፍፒን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ስምንቱ ሩዋንዳውያን ወደ ኒጀር እንዲሄዱ ሲደረግ የሩዋንዳ መንግስት ቅር ተሰኝቶ እንደነበር ጄዩን አፍሪክ የተባለ መጽሔት ያስነበበ ሲሆን ዜጎቹም ከኒያሚ እንዲወጡ ተደርጓል ተብሏል፡፡
ትዕዛዙ በኒጀር የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሃማዱ አማዱ ሶሌይ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ዲፕሎማሲያዊ በሆኑ ምክንያቶች በኒጀር ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እንዳያገኙ ተደርጓል ነው የተባለው፡፡ ከኒጀር እንዲባረሩ ከተደረጉት ስምንት ሩዋንዳውያን መካከል አራቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩዋዳን ጉዳይ ለማየት በተቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ወንጀል በተፈፀመባቸው ወንጀሎች የተከሰሱ ናቸው፡፡
የቀድሞ የሀገሪቱ ወታደራዊ መረጃ ኃላፊ፤ የቀድሞ የጦር መኮንንን ጨምሮ አራቱ ተከሳሾች የተፈረደባቸውን የእስራ ቅጣት ማጠናቀቃቸው ተሰምቷል፡፡ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወንድም፤ የቀድሞ ትራንስፖርት ሚኒስትር፤ እንዲሁም የቀድሞው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ከኒጀር እንዲባረሩ ከተደረጉት መካከል እደሚገኙ ተገልጿል፡፡
እነዚህ ስምንት ሩዋንዳውያን ከኒጀር እንዲወጡ የሰባት ቀናት ጊዜ ብቻ ተሰጥቷቸዋል ነወ የተባለው፡፡ ከሀገር እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ስምንቱ ሩዋንዳውያን ለምን ከሀገር እንደሚወጡ የተሰጠ ዝርዝር እንደሌለም ተገልጿል፡፡ የኒጀር የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ስለዚህ ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል ነው የተባለው፡፡
በፈረንጆቹ ኅዳር 15 ፣ ኒጀር ከግዛቷ እንዲወጡ ትዕዛዝ ያወጣችባቸውን ስምንት ሩዋንዳውያንንና የቀድሞ የሩዋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ለማስተናገድ ስምምነት ተፈራርማ ነበር፡፡ የቀድሞ የሩዋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሀገሪቱን ዘር ፍጅት ለመዳኘት ተቋቁሞ በነበረው ልዩ ፍርድ ቤት ነጻ መባላቸው ይታወሳል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1994 በሩዋንዳ ፅንፈኛ ሁቱዎች በቱትሲ ጎሳዎች ላይ በከፈቱት የዘር ጥቃት ከ800 ሺ በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል፡፡ ይህም በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተፈጸሙ ወንጀሎች አስከፊው እንደሆነ በርካቶች ይገልጻሉ፡፡