በሩዋንዳ ጭፍጨፋ ወቅት ወታደራዊ አመራር ይሰጡ የነበሩ ከፍተኛ ኮማንደር በእስር ቤት ህይወታቸው አለፈ
ኮለኔል ቲዮንስቴ ባጎሶራ የተበለው ይህ ሰው ሞት ፍርድ ተፈርዶበት ነበር
ባጎሶራ ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ለ800 ሺህ ሩዋንዳዊያን ሞት ዋነኛ ተጠያቂ ነበር
በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ወቅት ወታደራዊ አመራር ይሰጡ የነበሩ ከፍተኛ ኮማንደር በአስር ቤት ህይወታቸው አለፈ።
ከ27 ዓመት በፊት በምስራቅ አፍሪካዋ አገር ሩዋንዳ ሁቲ እና ቱትሲ በተሰኞ ጎሳዎች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ተከስቶ 800 ሺህ ዜጎች ተገድለው ክስተቱ እስካሁን ለዘር ፖለቲካ በማስተማሪያነት ይጠቀሳል።
ይህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በወቅቱ ስልጣን ላይ በነበሩ አመራሮች መደገፉ ብዙ ዜጎች ህይወታቸውን እንዲያጡ ዋነኛው ምክንያት ነበር።
በዚህ ዘግናኝ የሰው ልጅ ጭፍጨፋ በወቅቱ በአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የነበሩት ቲዮንስቴ ባጎሶራ ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ድጋፍ በተደረገው የምርመራ ሪፖርት መሰረትም ኮለኔል ባጎሶራ የዘር ጭፍጨፋውን በመምራት እና በማስተባበር ተሳትፈዋል መባላቸውን የሮይርስ ዘገባ ያስረዳል።
በዚህ መሰረትም ኮለኔል ባጎሶራ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ቆይቶ በተደረገ ይግባኝ እስሩ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮላቸው በማሊ መዲና ባማኮ ባለ እስር ቤት ቀሪ ጊዜያቸውን በማሳለፍ ላይ ነበሩ።
ኮለኔሉ በእስር ቤት ቆይታቸው ከሰባት ጊዜ በላይ ታመው ሶስት ጊዜ የቀዶ ጥገና ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን በተደጋጋሚ ይታመሙ እንደነበር ዘገባው አክሏል።
የልብ ህመም ለኮለኔሉ መሞት ዋነኛ መንስኤ ነበር የተባለ ሲሆን የኮለኔል ባጎርሶ ልጅ በሆስፒታል ውስጥ ህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው ማለፉን ልጃቸው ለመገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።
ኮለኔል ባጎርሶ ባቀነባበሩት ጥቃት የወቅቱ የሩዋንዳ ፕሬዘዳንት ጁቬናል ሃባሪማ ይጓዙበት የነበረው አውሮፕላን ተመቶ በመከስከሱ ፕሬዘዳንቱን ጨምሮ አብረው ተሳፍረው የነበሩት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
ከዚህ አደጋ በኋላም በሩዋንዳ የእርስ በርስ ጦርነት ተከስቶ 800 ሺህ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል።
በፖል ካጋሜ ይመራ የነበረው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር አገሪቱን መቆጣጠሩን ተከትሎ ኮለኔል ባጎርሶ በሸሹበት ካሜሩን ተይዘው ወደ ዘብጥያ ወርደዋል።
በፈረንጆቹ 2008 ዓመት ኮለኔል ባጎርሶ በሩዋንዳ በፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የ35 ዓመት እስር የተፈረደባቸው ሲሆን ቆይተው በተጣሩ ሌሎች ምርመራዎች ደግሞ ኮለኔሉ የሞት ፍርድ ቢበየንባቸውም ወደ አድሜ ልክ እስራት ሊቀየርላቸው ችሏል።
ይሁንና ኮለኔል ባጎርሶ ከሌሎች የቀድሞ የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር የተፈረደባቸውን የእስራት ጊዜ በመወጣት ላይ እያሉ በ89 ዓመታቸው በልብ ህመም ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።