የኒጀር ፕሬዝዳንት ከመፈንቅለ መንግስት በኋላ ዲሞክራሲን ለመታደግ ቃል ገቡ
ወታደሮች ፕሬዝዳንት ባዞም ከስልጣን መወገዳቸውን በብሄራዊ ቴሌቪዥን አውጀዋል
የወታደሩ መሪው ማን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም
የኒጀር ፕሬዝዳንት ከመፈንቅለ መንግስት በኋላ ዲሞክራሲን ለመታደግ ቃል ገቡ።
የኒጀር ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዞም በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ከተወገዱ ከአንድ ቀን በኋላ "በልፋት የተገኘ" ዲሞክራሲን ለመጠበቅ ማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ቃል ገብተዋል።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃሱሚ ማሱዱ መፈንቅለ መንግስቱ እንዲከሽፍ "ሁሉም ዲሞክራቶች እና አርበኞች" ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
መግለጫዎቹ ወታደሮች ፕሬዝዳንት ባዞም ከስልጣን መወገዳቸውን በብሄራዊ ቴሌቪዥን ማወጃቸውን ተከትለው የወጡ ናቸው።
የኒጀር መፈንቅለ መንግስት ከፈረንጆቹ 2020 ወዲህ በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሰባተኛው ነው።
ረቡዕ ዕለት የፕሬዝዳንቱ የጥበቃ አባላት በዋና ከተማዋ ኒያሚ የሚገኘውን ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት ተቆጣጥረዋል።
ወታደሮቹ ባዞምን እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጋቸው ሳህል ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን አማጽያን ለመዋጋት ለምዕራባውያን ዋነኛ አጋር በሆነችው ሀገር ስጋትን ደቅኗል።
ሀሙስ ጠዋት ዜጎች ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ኒያሜ ጸጥ ረጭ ማለቷ ተነግሯል። ድንበሮች የተዘጉ ሲሆን፤ ወታደሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰዓት እላፊ አውጇል።
የወታደሩ መሪው ማን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
የፕሬዝዳንቱ ጥበቃ በጄኔራል ኦማር ቲቺያኒ የሚመራ ቢሆንም፤ በቴሌቭዥን የተላለፈውን መግለጫ ግን ኮሎኔል አማዱ አብድራማኔ በተባሉ የአየር ኃይል አባል ነው የተነበበው።