ወታደሮቹ በኒጀር ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ እስኪመለስ ድረስ ሁሉንም የህግ አውጭና አስፈጻሚ ስልጣንን እንረከባለን ብለዋል
የኒጀር የመፈንቅለ መንግስት መሪዎች ጄኔራል አብዱራሃማኔ ቲያኒን አዲስ "ፕሬዝዳንት" አድርገው አውጀዋል።
ከሦስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ሰባተኛው በሆነው መፈንቅለ መንግስት፤ ፕሬዝደንት መሀመድ ባዙም በወታደሩ ከስልጣን ተወግደዋል።
የአፍሪካ ሀገሮች፣ ምዕራባውያን፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለፕሬዝዳንት ባዙም ድጋፋቸውን ገልጸው፤ ዴሞክራሲ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ጠይቀዋል።
ጄኔራል ቲያኒ የፕሬዝዳንቱ የጥበቃ ኃላፊ ነበሩ። ረቡዕ ዕለት ወታደሮቹ ባዙምን ቤተ መንግስት ውስጥ ያገቱ ሲሆን፤ ይህም መንበሩን ማን እንደተቆጣጠረው ግራ መጋባት ፈጥሯል።
ባዙም በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ በትግል የተገኘን ዲሞክራሲ ለማስጠበቅ እንደሚታገሉ ቃል ከገቡ ወዲህ ድምጻቸው አልተሰማም።
በርካታ የዓለም መሪዎች መፈንቅለ መንግስቱ ከተካሄደበት ጊዜ ጀምሮ እንዳነጋገሯቸውና አሁንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በቤተ መንግስት ውስጥ እንደታሰሩ ተናግረዋል።
የኒጀር የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ባዙምን አሁንም ህጋዊ መሪ ናቸው ስትለሰ እውቅና መስጠቷን ተናግራለች።
ጄኔራሉ አርብ ዕለት በመንግስት ቴሌቭዥን ቀርበው አዲስ የተቋቋመው ወታደራዊ አካል "የሀገር ውስጥ ጥበቃ ብሄራዊ ም/ቤት" ፕሬዝዳንት መሆናቸውን የሚገልጽ ባነር ይዘው ታይተዋል።
"የም/ቤቱ ፕሬዝደንት የሀገር መሪ ነው" ሲሉ አንድ ባለስልጣን በመግለጫው ተናግሯል።
"ህገ መንግስቱ ታግዷል፤ ሁሉም የመንግስት ተቋማት ፈርሰዋል። ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ እስኪመለስ ም/ቤቱ ሁሉንም የህግ አውጭና አስፈጻሚ ስልጣን እንጠቀማለን" ብለዋል።
ሆኖም ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ የጊዜ ገደብ አልተሰጠም።