አሜሪካ በኒጀር 1 ሺህ ወታደሮቿን አስፍራለች
ኒጀር ከአሜሪካ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር አቋረጠች፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር ባሳለፍነው ዓመት በምርጫ ተመርጠው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት መሀመድ ባዙም በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን በሀይል መነሳታቸው ይታወሳል፡፡
በጀነራል አብዱራህማን ትቺያኒ የተመራው ይህ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከተቆጣጠረ ዓመት ያለፈው ሲሆን ከቀድሞ ቅኝ ገዚዋ ፈረንሳይ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋርጧል፡፡
ፈረንሳይም በኒያሚ የነበራትን ጦር ያስወጣች ሲሆን አሁን ደግሞ ከአሜሪካ ጋ የነበረውን ወታደራዊ ስምምነት አቋርጧል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ አሜሪካ ይህንን ወታደራዊ ስምምነት ለማስቀጠል ከሰሞኑ ልዑካኗን ወደ ኒያሚ ልካ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የጀነራል ትቺያኒ ወታደራዊ መንግስት ከአሜሪካ ጋር የነበረው ወታደራዊ ስምምነት መቋረጡን በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ይፋ አድርጓል፡፡
ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ የአጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
ኒጀር የአሜሪካ ወታደሮች በሀገሯ እንዲሰፍሩ እና ወታደራዊ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የሚፈቅድ ህግ ያላት ቢሆንም ስምምነቱ እንደማይቀጥል አስታውቃለች፡፡
አሜሪካ አሁን ላይ 1 ሺህ ወታደሮችን በኒጀር ያሰፈረች ሲሆን ለዚህ ወታደራዊ ማዘዣ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከአንድ ዓመት በፊት ኒጀርን የጎበኙ ቢሆንም ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኒያሚ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዷል፡፡
ኒጀር ከመፈንቅለ መንገስቱ በኋላ ከምዕራባዊን ሀገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ የመጣ ሲሆን ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት ደግሞ እየጠነከረ ስለመምጣቱ ይገለጻል፡፡
ኒጀር በዩራኒየም ማዕድን ሀብታም ከሆኑ ጥቂት የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ አይዘነጋም፡፡