ኒጀር ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ያደረገችው
አዲሱ የኒጀር ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም በዛሬው እለት ቃለ መሃላ መፈጸማቸው ተነግሯል።
ኒጀር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1960 በቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ያደረገችበት እልት ሆኖም ተመዝቧል።
የዛሬው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር በበረካታ ፈተናዎች ውስጥ ማለፉ የሚነገርለት ሲሆን፤ ባሳለፍነው ረቡዕ የተሞከረው መፈንቅለ መንግስትም ከፈተናዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
በተጨማሪም ኒጀር ከማሊ ጋር በምትዋሰንባቸው ድንበር አካባቢ በአክራሪ የሽብር ቡድኖች በርክታ የጸጥታ ችግሮችን እንደምታስተናግድም ይታወቃል።
አዲሱ የኒጀር ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “የአሸባሪ ቡድኖች ጭቃኔ ከገደብ አልፏል፤ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ እየፈጸሙ ነው፤ ተግባራቸውም ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ነው” ብለዋል።
“የሽብር ቡድኑ መሪዎች የሌላ ሀገር ዜጎች ናቸው፤ ስለዚህ ኒጀር ያለ ምንም ምክንያት ነው እየተጠቃች ያለቸው” ሲሉም ተናግረዋል።
የሽብር ቡድን አባላቱ ማእከላቸውን ማሊ ላይ በማድረግ ኒጀርን የሚያጠቁ ሲሆን፤ ይህንን ለማስቆምም “የኒጀር ዲፕሎማሲ ማእከል ማሊ ትሆናለች” ሲሉም ፐሬዚዳነቱ በንግግራቸው አንስተዋል።
የቀድሞው የኒጀር የውጭ ጉዳይ እና የሀገር ውስጥ ሚኒስትር መሐመድ ባዙም በሀገሪቱ በሁለት ዙር በተካሄደ ምርጫ ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ገዥውን ፓርቲ ወክለው ለምርጫ ቀርበው የነበሩት ባዙም በምርጫው ከተሰጠው ድምጽ 55.75 በመቶ በላይ የሚሆነውን በማግኘት ማሸነፋቸውም ተነግሯል።