ተገኘ የተባለው ተጨማሪ የጋዝ ክምችት 206 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ይደርሳል ተብሏል
ድፍድፍ ነዳጅን ስትፈልግ የነበረችው ናይጄሪያ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተጨማሪ 206 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የጋዝ ክምችት ማግኘቷን አስታወቀች፡፡
ክምችቱ በአጋጣሚ መገኘቱን የሃገሪቱ የፔትሮሊዬም ሚኒስትር ዴዔታ ቲምፕሬ ሲልቫ ትናንት ቅዳሜ አስታውቀዋል፡፡
ይህ ተጨማሪ ፍለጋዎችን ብናደርግ እስከ 600 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የጋዝ ክምችትን ለማግኘት እንደምንችል የሚያሳይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ክምችቱ በነዳጅ የበለጸገ ሃገር ሊኖረው የሚችለውን የእድገት ደረጃ ለማሳካት የሚያስችል ነው ሲሉ ለሃገሪቱ ዜና አገልግሎት (NAN) ተናግረዋል፡፡
ዜና አገልግሎቱን ዋቢ እንዳደረገው እንደ ኬንያው ተነባቢ ጋዜጣ ‘ኔሽንስ’ ዘገባ ናይጄሪያ እ.ኤ.አ በ2017 የተረጋገጠ 187 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የጋዝ ክምችት ነበራት፡፡
ክምችቱ በዓለም የ9ኛ ደረጃን ያሰጣትና 3 በመቶው የዓለማችን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በናይጄሪያ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነበር፡፡ ከዚያም ወዲህ ክምችቱ እያደገ መጥቷል፡፡ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት (2020) የአሁኑን ግኝት ሳይጨምር 203 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ደርሶ እንደነበርም ዘገባው ያትታል፡፡
ይህ መሆኑ ሃገሪቱ ወደ ታዳሽ ኃይል የምታደርገው የኢነርጂ ሽግግር ለማሳካት እንደሚያስችል ቲምፕሬ ሲልቫ ተናግረዋል፡፡
ናይጄሪያ ከፍተኛ የጋዝ ክምችት አላት ይባል እንጂ እምብዛም ጋዝን ለቤት ውስጥ ፍጆታም ሆነ ለኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት አትጠቀምም፡፡ ብዙሃኑ ናይጄሪያዊም በነዳጅ ሊደገፉ የሚችሉ የኤሌክትሪክ ግልጋሎቶችን አያገኝም፡፡
ይህን ለመቅረፍ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች ይሰራሉም ነው ሚኒስትሩ ያሉት፡፡