ግለሰቦች ለመድሃኒትነት ይጠቅማል የተባለ ከዕፅዋት የተቀመመ መጠጥ ጠጥተው ነው ህይወታቸው ያለፈው
በናይጄሪያዋ ክዋራ ግዛት “ከዕፅዋት የተቀመመ” ነው የተባለ መጠጥ የጠጡ 10 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ።
ግለሰቦቹ መጠጡን የጠጡት በእግር ላይ ለሚከሰት ህመም መድሃኒት ነው ተብለው እንደሆነ የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል።
የክዋራ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ አጃይ ኦካሳምኒ፤ ከዕፅዋት የተቀመመውን መጠጥ ጠጥተው ህይወታቸው ያለፈ 10 ሰዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው ብለዋል።
ሁለት የቤተሰቡ የቅርብ ጓደኞች ከዕፅዋት የተቀመመው መጠጥ ለጤና ጠቃሚ ነው ካሏቸው በኋላ ጠጥተው ሕይወታቸው ማለፉንም ነው ቀል አቀባዩ ያስታወቁት።
መጀመሪያ በአንድ የቤተሰቡ አባል ላይ የእግር ህመም መከሰቱን እና መጠጡ ለዚህ ጠቃሚ እንደሆነ፤ ህመሙ ወደ ሌሎችም እንዳይተላለፍ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ሊጠጣው እንደሚገባ መምከራቸውንም ፖሊስ አስታውቋል።
መድሃኒት ነው የተባለውን መጠጥ ከጠጡ በኋላም እግሯ የታመመውን የቤተሰቡን አባል ጨምሮ አስሩም ሰዎች አንድ በአንድ ህይወታቸው ማለፉም ነው የተነገረው።
የቤተሰቡ አባላት መጠጡን እንዲጠጡ አድርገዋል የተባሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ እንደሆነም ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ምርመራውን እንዳጠናቀቀም ግለሰቦች ፍድር ቤት የሚቀርቡ ይሆናል ተብሏል።