ናይጀሪያ አሜሪካ የሽብር ጥቃትን አስመልክቶ ያወጣችው መረጃ ሀላፊነት የጎደለው ስትል ኮነነች
አሜሪካ ባለፈው ሳምንት በሌጎስ የሽብር ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቃ ነበር
አሜሪካንን ጨምሮ ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ አየርላንድ እና አውስትራልያ ዜጎቻቸው ሌጎስን እንዲለቁ አሳስበው ነበር
ናይጀሪያ አሜሪካ የሽብር ጥቃትን አስመልክቶ ያወጣችው መረጃ ሀላፊነት የጎደለው ስትል ኮነነች፡፡
አሜሪካ ከሰሞኑ በናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም ስለሚችል ዜጎቿ ናይጀሪያን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቧ ይታወሳል፡፡
የአሜሪካን የደህንነት ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ፕሬዝዳንት መሀማዶ ቡሃሪ የሀገሪቱን የደህንነት ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ስለ ናይጀሪያ ጸጥታ ጉዳይ መምከራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላም የናይጀሪያ መዲና አቡጃን ጨምሮ የሀገሪቱ ደህንነት በአስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቃለች፡፡
የፕሬዝዳንት ቡሃሪ የደህንነት አማካሪ ባባጋና ሙንጉኖ እንዳሉት የአሜሪካ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ሃላፊነት የጎደለው እና አላስፈላጊ ድርጊት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቡጃ ከተማ በናይጀሪያ የጸጥታ መዋቅር ቁጥጥር ስር መሆኗን የተናገሩት አማካሪው የአሜሪካ የደህንነት ማስጠንቀቂያ የተጋነነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የናይጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጎድፌሬይ ኦኒያማ በበኩላቸው ሀገራቸው ከምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ስለ አቡጃ ደህንነት የተጣራ መረጃ እንዲኖራቸው በጋራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በናይጀሪያ ጉዳይ የሚያወጡት መረጃ የባሰ ጉዳትን የማያመጣ ሊሆን ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ ትብብራቸ ንም ይሄንን መሰረት ባደረገ መንገድ ብቻ ይሆናል ሲሉም አክለዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ከአሜሪካ በተጨማሪ ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ አየርላንድ እና አውስትራሊያ ዜጎቻቸው በናይጀሪያ የሽብር ጥቃት ስጋት ስላለ በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ አሳስበው ነበር፡፡
ሀገራቱ በዚህ የደህንነት ማስጠንቀቂያቸው የሽብር ድርጊት፣ እገታ እና ገንዘብ ጥየቃ ወንጀሎች በታጣቂዎች ሊፈጸሙ ይችላሉ ሲሉ በማስጠንቀቂያቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
አራቱ ሀገራት ከናይጀሪያ መንግስት በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካም ተመሳሳይ ወንጀሎች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ በመግለጫቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡