ናይጀሪያ አማጺ ቡድኖችን የሚያጀግኑ ዘገባ ባሰራጩ ሚዲያዎች ላይ ቅጣት ጣለች
በናይጀሪያ መንግስት ቅጣት ከተጣለባቸው ሚዲያዎች መካከል ዲኤስቲቪና ትረስት ቲቪ ዋነኞቹ ናቸው
ሚዲያዎቹ እያንዳንዳቸው 12 ሺህ ዶላር እንዲከፍሉ ቅጣት ተጥሎባቸዋል
ናይጀሪያ ቢቢሲ የአማጺ ቡድኖችን በሚያጀግን መልኩ የሰራውን ዘገባ ባሰራጩ ሚዲያዎች ላይ ቅጣት ጣለች።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጀሪያ ቦኮሀራም የሽብር ቡድንን ጨምሮ በአማጺ ቡድኖች ጥቃት እየተፈተነች ሲሆን የጸጥታ ስጋቱ እስከ ሀገሪቱ መዲና ሌጎስ ዘልቋል።
የአማጺ ቡድኖቹ ጥቃት እንዳለ ሆኖ ሚዲያዎች የናይጀሪያ ዜጎች ከሀገሪቱ የጸጥታ መዋቅር ይለቅ በአማጺ ቡድን መሪዎች እንዲተማመኑ የሚያደርጉ ዘገባዎችን ከመስራትና ከማስራጨት እንዲቆጠቡ ስታሳስብ ቆይታለች።
ቢቢሲ ባሳለፍነው ሳምንት በሰሜናዊ ናይጀሪያ ባለችው ዛምፋራ ግዛት ህጻናትን ከሚማሩበት ትምህርት ቤቶች በማገት እና ሌሎች አደጋዎችን በንጹሃን ላይ በማድረስ የሚከሰሰውን አንድ አማጺ ቡድን የሚያጀግን ዘገባ ለተመልካቾቹ አስተላልፏል በሚል በሀገሪቱ መንግስት ክስ ቀርቦበታል።
ይህ ዘገባ መተላለፉን ተከትሎ ጉዳዩ በናይጀሪያ ዋነኛ መነጋገሪያ የነበረ ሲሆን በድርጊቱ የተቆጣው የናይጀሪያ መንግስት የዘገባውን ሚዛናዊነት እና አሰራር እንደሚመረምር አስጠረንቅቆ ነበር።
የናይጀሪያ ሚዲያ ምዝገባ እና ቁጥጥር ባለስልጣን አማጺ ቡድኖችን የሚያጀግኑ ዘገባዎችን በማሰራጨት የተከሰሱ ሶስት ሚዲያዎች ላይ የገንዘብ ቅጣት ማስተላለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቅጣቱ የተላለፈባቸው ሚዲያዎች በመልቲ ቾይዝ ናይጀሪያ ስር የተመዘገበው ዲኤስቲቪ፣ ቴሌኮም ሳተላይት እና በናይጀሪያ መንግስት እና በቻይናው ስታር ታየምስ በተሰኙ ሶስት የሚዲያ ተቋማት ናቸው።
እነዚህ ሚዲያዎች እያንዳንዳቸው 12 ሺህ ዶላር እንዲከፍሉ ቅጣት እንደተጣለባቸውም ዘገባው አክሏል።
እንዲሁም ትረስት ቴሌቪዥን የተሰኘ ሀገር በቀል ሚዲያ አማጺ ቡድኖችን የሚያጀግኑ ዘገባዎችን ሰርቷል በሚል በተመሳሳይ 12 ሺህ ዶላር ቅጣት ተወስኖበታል ተብሏል።
እንደ ሀገሪቱ ሚዲያ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መግለጫ ከሆነ እነዚህ ሚዲያዎች ከሚዲያ ህጉን በመጣስ ናይጀሪያዊያንን የሚከፋፍል፣ የሕግ የበላይነት እንዳይሰፍን እና አማጺ ቡድኖችን የሚያነቃቁ ይዘት ያላቸውን ዘገባዎች ሆን ብለው አሰራጭተዋል።
ቢቢሲ ባሳለፍነው ሳምንት ተመሳሳይ ይዘት ያለው ዘገባ ማሰራጨቱን ተከትሎ የናይጀሪያ መንግስት ዘገባውን እንደሚመረምር እና እርምጃ እንደሚወስድ ማሳወቁ ይታወሳል።
የናይጀሪያ መንግስት አክሎም ጉዳዩ ሚዲያዎችን በማስፈራራት መዝጋት እና ሌሎች ተጽዕኖዎችን ማድረግ አይደለም ያለ ሲሆን የተቀመጡ የአሰራር ህጎች መፈጸማቸውን ማረጋገጥ እንደሆነ አስታውቋል።
በናይጀሪያ የተለያዩ አማጺ ቡድኖች በሚያደርሱት ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲሞቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል።