ናይጄሪያ በሀገሯ ያሉ የውጭ አየር መንገዶችን 450 ሚሊየን ዶላር አገደች
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር በበኩሉ ናይጄሪያ ገንዘቡን ባስቸኳይ እንድትለቅ አሳስቧል
ኢትዮጵያም የውጭ አየር መንገዶችን ገንዘብ ካልከፈሉት ሀገራት መካከል አንዷ ናት
ናይጄሪያ በሀገሯ ያሉ የውጭ አየር መንገዶችን 450 ሚሊዮን ዶላር አገደች፡፡
የዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ማህበር ዓመታዊ ስብሰባውን በኳታር መዲና ዶሃ በማካሄድ ላይ ሲሆን በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ፈተናዎች እና እድሎች ዙሪያ ከአየር መንገዶች ስራ አስኪያጆች ጋር እየመከረ ነው፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጄሪያ በሀገሯ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የውጭ ሀገራት አየር መንገዶችን ገንዘብ አለመክፈሏን ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ማህበር አስታውቋል፡፡
አየር መንገዶቹ በናይጄሪያ ውስጥ እና ከሌሎች ሀገራት ወደ ናይጄሪያ መንገደኞችን እና እቃዎችን በማጓጓዝ አገልግሎት ከደንበኞቻቸው የሰበሰቡትን 450 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንዳይችሉ መታገዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
በማህበሩ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ምክትል ፕሬዝዳንት የሖኑት ከማል አል አዋዲ ለሮይተርስ እንዳሉት ናይጀሪያ የአየር መንገዶቹን ገንዘብ ማገዷን ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ በጉዳዩ ዙሪያ ከናይጀሪያ ማዕከላዊ ባንክ ጋር ሁለት ጊዜ መወያየታቸውን ገልጾ ሀገሪቱ ይሄንን ያደረገችው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ስላጋጠማት እንደሆነ መስማታቸውን አል አዋዲ ገልጸወል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም የናይጄሪያ መንግስት ድርጊት የሀገርን መልካም ገጽታ የሚያበላሽ እና አየር መንገዶች በቀጣይ እንዳይበሩ ሊያደርግም ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ናይጄሪያ ከዚህ በፊት በሀገሯ የነበሩ የውጭ ሀገራት አየር መንገዶችን ሀብት አግዳ የነበረ ሲሆን በተደረገ ተደጋጋሚ ጥያቄ ገንዘባቸውን ከፍላ ነበር ተብሏል፡፡
ገንዘባቸው በናይጄሪያ መንግስት የተያዘባቸው የውጭ ሀገራት አየር መንገዶቹ ወኪሎች ቀጣይ ውይይታቸውን በቅርቡ ለመጀመር በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ዘገባው አክሏል፡፡
አፍሪካ እስካሁን የዓለም አቀፍ አየር መንገዶች 1 ቢሊዮን ዶላር እዳ እንዳለባት ማህበሩ የገለጸ ሲሆን ናይጄሪያ ትልቁ እዳ ያለባት ሀገር መሆኗንም አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ፣አልጄሪያ ፣ኤርትራ እና ዚምባብዌ በድምሩ 271 ሚሊየን ዶላር የዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ገንዘብ ያለባቸው ሀገራት ናቸውም ተብሏል፡፡