የጦር አውሮፕላኖቹ ከራዳር እይታ ውጪ በመብረር ቦኮሀራምን ለመደምሰስ ያገለግላሉ ተብሏል
ናይጀሪያ ስድስት የጦር አውሮፕላኖችን ከአሜሪካ መረከቧ ተሰምቷል።
አገሪቱ እነዚህን የጦር አውሮፕላን ከአሜሪካ የተረከበችው በግዥ ነው።
ናይጀሪያ በፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመን ከአሜሪካ የሽብርተኞችን ጥቃት ለመመከት እና ለማስወገድ A -29 የተሰኘውን ዘመናዊ የጦር አውሮፕላን ለመግዛት ስምምነት ፈጽማ ነበር።
ይሁንና የናይጀሪያ አየር ሀይል በስህተት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን በቦንብ በመደብደቡ ምክንያት የጦር መሳሪያ ግዥው እንዲሰረዝ ተደርጎ ነበር።
ፕሬዘዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣታቸወን ተከትሎ የጦር መሳሪያ ግዥው በድጋሜ ወደ ስራ እንዲገባ ተወስኖም ነበር።
እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ ናይጀሪያ በትናንትናው ዕለት ስድስት ቀላል እና ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችን ተረክባለች።
እነዚህ የጦር አውሮፕላኖች ከእይታ ውጭ የሆኑ የአየር ላይ ጥቃት አድራሽ የጦር ጀቶችን ለማውደም፤ የስለላ እና ሌሎች የሽብር ጥቃቶችን ለመመከት እንደሚያግዝ በዘገባው ተጠቅሷል።
ናይጀሪያ ከዚህ በፊት ከአሜሪካ ጋር በፈጸመቸው የጦር መሳሪያ ግዢ ስመምነት መሰረት በ593 ሚሊየን ዶላር 12 የጦር አውሮፕላን፤ሮኬቶች፤ቦንቦችን እና ሌሎች ወታደራዊ ስልጠና ለማድረግ ተስማምታ ነበር።
አሁን ላይ ናይጀሪያ ከተረከበችው ስድስት የጦር አውሮፕላኖች በተጨማሪ ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ይኑሩ አይኑሩ እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።
ናይጀሪያ አሁን ላይ በቦኮሀራም የሽብር ቡድን ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት እየተፈጸመባት ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የተማሪዎች እገታ ፤ወታደራዊ የጦር ካምፖች ጥቃት እና የጦር አውሮፕላኖች ጥቃቶችን እያስተናገደች ትገኛለች።