በናይጄሪያ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ የሀገር ውስጥ በረራዎች ተቋረጠ
ዘጠኝ የናይጄሪያ የአቪዬሽን ተቋማት ህብረት በጋራ ባወጡት መግለጫ የነዳጅ ዋጋ ለ 4ኛ ጊዜ ጭማሪ አሳይቷል
መንግስት እነዚህ አየር መንገዶች ላለፉት አራት ወራት የነዳጅ ድጎማ ሲያደርግላቸው ቆይቷል
በነዳጅ ሀብቷ ከአፍሪካ አንደኛ የሆነችው ናይጀሪያ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ የሀገር ውስጥ የአውሮፕላን በረራዎች መቋረጣቸው ተገለፀ።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናይጄሪያ ዘጠኝ የአቪዬሽን ተቋማት የሀገር ውስጥ በረራ አገልግሎትን ለዜጎች በመስጠት ላይ ነበሩ።
የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ከገባ በኋላ አራ ጊዜ የአውሮፕላን ነዳጅ መጨመሩን የሚናገሩት እነዚህ የናይጀሪያ አቪዬሽን ተቋማት አሁን ግን አገልግሎቱን ከነገ በስቲያ ማለትም ከሰኞ ጀምሮ እንደሚያቋርጡ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የናይጀሪያ መንግስት ለነዚህ አቪዬሽን ተቋማት የነዳጅ ድጎማ ሲያደርግ ቢቆይም ድጎማው ከኪሳራ ሊያድናቸው አለመቻሉንም ገልጸዋል።
አየር መንገዶቹ ከዚህ በፊት በነዳጅ እጥረት ምክንያት በርካታ በረራዎችን መሰረዛቸው የተገለጸ ሲሆን የጉዞ ቲኬት ዋጋም ከሶስት እጥፍ በላይ መጨመሩ ተገልጿል።
ናይጀሪያ በውጭ ምንዛሬ እየተፈተነች ሲሆን አየር መንገዶች ደግሞ የጉዞ ቲኬት ለደንበኞች በዶላር እንዲከፍሉ በማስገደድ ላይ ናቸውም ተብሏል።
ናይጀሪያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የነዳጅ ባለቤት ብትሆንም የአውሮፕላን ነዳጅ ፍላጎቷ ግን ሙሉ በሙሉ ከውጭ ሀገራት ታስገባለች።
በናይጀሪያ ቦኮሀራምን ጨምሮ ሌሎች የሽብር ቡድኖች በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው በባቡር እና በተሸከርካሪ የሚደረጉ ጉዞዎችን አስቸጋሪ እያደረገው እንደሆነ ዘገባው አክሏል።