የኑሮ ውድነትና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በመላው ናይጀሪያ ተቃውሞ አስነስቷል
በዛሬው እለት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መካሄድ የጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ለሚቀጥሉት አስር ቀናት ይቀጥላል ተብሏል
በናይጀሪያ የነዳጅ ድጎማ መነሳቱን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በሶስት እጥፍ መጨመሩ ተገልጿል
ከአፍሪካ በህዝብ ቁጥር አንደኛ በሆነችው ናይጀሪያ የኑሮ ውድነትን እና የነዳጅ ዋጋ መጨመርን የሚቃወም ሰልፍ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ተግባራዊ ባደረጉት የኢኮኖሚ ማሻሻያ የነዳጅ ድጎማን በማንሳት የሀገሪቱን ገንዘብ ናይራ የመግዛት አቅም እንዲዳከም አድርገዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የዋጋ ንረት ያማረራቸው ናይጄሪያውያን የሀገሪቱ መንግስት ማሻሻዎችን እንዲያደርግ በሰላማዊ ሰልፍ እየጠየቁ ነው፡፡
የነዳጅ ድጎማው ከተነሳ ወዲህ የነዳጅ ዋጋ በሶስት እጥፍ የጨመረ ሲሆን በሀገሪቱ የሚገኝው የምግብ የዋጋ ንረት በ በ40 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ አመት በሀገሪቱ የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ንረት ከ30 አመታት ወዲህ ከፍተኛው ነው፡፡
ውጥረቱን ለመቀነስ የሀገሪቱ መንግስት በትላንትናው እለት ከውጭ ሀገር ስንዴ በማስገባት በጣም ለተቸገሩ ዜጎች አከፋፍሏል፡፡ በተጨማሪም የአነስተኛ የደመወዝ ወለልን መነሻ ከፍ እንደሚያደርግም አሳውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ለሳምንታት “በናይጄርያ ያለው መጥፎ አስተዳደር ሊያበቃ ይገባል” በሚል መሪ ቃል በማህበራዊ ትስስር ገጾች ጥሪ ሲከናወንበት የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ ሊቆም አልቻለም፡፡
ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ቢተኩስም በዛሬው አለት በዋና ከተማዋ አቡጃ እና ሌጎስን ጨምሮ በሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች በመካሄድ ላይ የሚገኘው የተቃውሞ ሰልፍ ለቀጣዮቹ አስር ቀናት ይዘልቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ መሪዎቹ በፖሊስ እና ሰልፈኞች መካከል የሚኖረውን ግጭት ለመቀነስ ከሰልፈኞቹ ጋር መግባባታቸውን ለመገናኛ ብዙሀን ተናግረዋል፡፡
ከአዘጋጆቹ መካከል አንዱ የሆነው ኦሞሎላ ፔድሮ ሰልፎቹ ወደ አመጽ እንዲቀይሩ አንፈልግም፤ ማድረግ የምንፈልገው በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማንችል መንግስት እንዲረዳልን ድምጻችንን ማሰማት ብቻ ነው ብሏል፡፡
ተቃዋሚዎቹ እንዲፈጸሙ የሚፈልጓቸውን 19 ፍላጎቶች በዝርዝር ያስቀመጡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የነዳጅ ድጎማ መልሶ ተግባራዊ ይሁን የሚለው ቀዳሚው ነው ብለዋል።
በተጨማሪም መንግስት የሚያወጣቸው ያልተገቡ ወጪዎች ኢኮኖሚው ላይ ጫና እያሳደሩ ስለሚገኙ መንግስት የውጭ ቅነሳ ተግባራዊ ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡
በተያዘው አመት መንግስት በ20.5 ቢሊየን ናይራ ፕሬዝዳንቱ የሚጠቀሙባቸው ሁለት አዳዲስ የግል አውሮፕላኖችን ፣ በ5 ቢሊየን ናይራ የፕሬዝዳንታዊ መርከብ ግዥ ፣ 61.29 ቢሊየን ናይራ ህንጻዎችን ለማስዋብ እና ለማደስ ፣ 6.82 ቢሊየን ዶላር አዳዲስ ተሸከርካሪዎችን ለመግዛት ገንዘብ አውጥቷል፡፡
ይህ ገንዘብ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እና ምርታማነትን በሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ላይ መዋል ሲገባው የመንግሰት ቅንጡ ኑሮ እና ምቾት ለማርጋገጥ ውሏል ያሉት ናይጀሪያውያን በበጀት አጠቃቀም እና በመንግሰት ግዢ ላይ ግልጽ የሆነ አሰራር እንዲዘረጋ ነው የጠየቁት፡፡
የናይጀሪያ መንግስት ዜጎች በሰላማዊ መንግድ ሀሳባቸውን የመግለጽ መብት አላቸው ነገር ግን በኬንያ እንደታየው አመጻ ማስነሳት የሚፈልጉ አካላትን አንታገስም ብሏል፡፡