የ27 አመቱ ናይጄሪያዊ ለ9 ቀናት በማንበብ በአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ሰፈረ
በአንድ ሰአት ልዩነት 5 ደቂቃ ብቻ እረፍት በመውሰድ ለ9 ቀናት ያለማቋረጥ የተለያዩ መጽሀፍትን እየጮኸ አንብቧል
ወጣቱ በናይጄሪያ የንባብ ባህልን ለማበረታታት እንቅስቃሴዎችን ሲያደረግ መቆየቱ ተነግሯል
የ27 አመቱ ናይጄሪያዊ ሳምሶን አጃዎ ለ9 ቀናት ያለመቋረጥ እየጮኸ በማንበብ በአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሙን ማስፈር ችሏል፡፡
ንባብን በሚያበረታቱ የተለያዩ ማእቀፎች ላይ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ሳምሶን በናይጄሪያ የንባብ ባህል እንዲዳብር ፍላጎት እንዳለው ይናገራል፡፡
ወጣቱ 215 ሰአታት ወይም 9 ቀን ሊሞላው አንድ ሰአት በቀረው የንባብ ቆይታ 100 መጽሀፍትን አንብቧል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረውን ክብረ ወሰን ለመስበርም የፋይናንስ ፣ ቢዝነስ ፣ የአስተዳደር ፣ የፖለቲካ ፣ የሽያጭ እና የጤና ይዘት ያላቸውን መጽሀፍት ማንበቡ ነው የተገለጸው፡፡
ለመወዳደርያ የተጠቀመባቸውን መጽሀፍት ይዘቶች ለምን እንደመረጣቸው ሲጠየቅም የሰው ልጅ ህይወት ከጤና ፣ ከንግድ እና ከአስተዳደር ጋር በጥልቅ የተገናኝ በመሆኑ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ሳምሶን ለቀናት ያለማቋረጥ ድምጽ እያወጣ መጽሀፍትን ሲያነብ በአንድ ሰአት ልዩነት ውስጥ 5 ደቂቃ ብቻ እረፍት ያደርግ የነበረ ሲሆን የእረፍት ሰአቱን ምግብ ለመብላት ፣ መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም እና ልብሱን ለመቀየር ያውለው እንደነበር ተነግሯል፡፡
ክብረ ወሰኑን ለመስበር ሙከራ ከማድረጉ በፊት ከሀኪሞች ጋር ባደረገው ምክክር ምን አይነት ምግቦችን እና መጠጦችን ቢጠቀም ተጨማሪ ጉልበት ሊያገኝ እንደሚችል እንዲሁም የመጻዳጃ ቤት ምልልሱን ሊቀንሱ የሚችሉ የምግብ አይነቶች ዙርያ ምክር አግኝቷል፡፡
ሳምሶን የአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ እውቅናን ካገኘ በኃላ የእንቅልፍ ሁኔታ እና እየጮኸ በሚያነብበት ወቅት ጉሮሮው አካባቢ የሚሰማው ህመም ከባድ ቢሆኑም አላማውን ለማሳካት እንዳላገደው ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡
መጽሀፍትን ለቀናት ሳያቋርጡ የማንበብ ልማዶች በ1987 በእንግሊዛዊው አድሪያን ሂልተን የተጀመረ ሲሆን 110 ሰአታትን ያለማቋረጥ ማንበብ ችሏል፡፡
በ2008 ትወልደ ኔፓላዊው ዲፓክ ሻርማ 113 ሰአታት ከ15 ደቂቃ የንባብ ቆይታ ሲያስመዘግብ በ2022 ካዛኪስታናዊው ሬስባይ ኢሳኮቭ 124 ሰአታትን በማንበብ እስካሁን ክብረ ወሰኑን ይዞ ቆይቶ ነበር፡፡