ናይጀሪያ የዩንቨርሲቲ መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር ጾታዊ ግንኙት እንዳይጀምሩ የሚከለክል ህግ አወጣች
መምህራኑ ከተማሪዎቻቸው ጋር ጾታዊ ግንኙነት ከጀመሩ የ14 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል
ሕጉ ስራ ላይ እንዲውል አዲሱ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ መፈረም ያጠበቅባቸዋል
ናይጀሪያ ከተማሪዎቻቸው ጋር ጾታዊ ግንኙት የጀመሩ የዩንቨርሲቲ መምህራን በ14 ዓመት የሚቀጣ ህግ አወጣች፡፡
ተሰናባቹ የናይጀሪያ ህግ አውጪ ምክር ቤት ቦታውን ለአዲስ መጪ ምክር ቤት አባላት ከማስረከቡ በፊት አነጋጋሪ ህግ ማጽደቁ ተገልጿል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ በናይጀሪያ የዩንቨርሲቲ መምህራን ተማሪዎችን በግሬድ በማስፈራራት ጾታዊ ግንኙነት ማድረግ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡
ይህን የተረዳው የሀገሪቱ ተሰናባች ምክር ቤት የዩንቨርሲቲ መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር ጾታዊ ግንኙነት እንዳይመሰርቱ የሚከለክል ህግ አውጥቷል።
አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ይህን ህግ ፈርመው እንደሚያጸድቁት የሚጠበቅ ሲሆን በዚህ ህግ መሰረት መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር ጾታዊ ግንኙነት መስርተው ከተገኙ እስከ 14 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል፡፡
ይህ አነጋጋሪ ህግ በፈረንጆቹ 2016 ላይ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ውይይት ሲደረግበት እንደቆየ ተገልጿል፡፡
የናይጀሪያ አዲ የምክር ቤት አባላት በሚቀጥለው ሳምንት ቃለ መሀላ ፈጽመው ስራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡
የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች አዲስ በወጣህ ህግ መደሰታቸውን በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በመግለጽ ላይ ሲሆኑ ፕሬዝዳንት ቲኑቡ ፈርመው ወደ ተግባር እንዲውል ማድረግ ይጠብቅባቸዋልም ተብሏል፡፡