ዓለም አቀፉ ሚዲያ ቢቢሲ ሰራተኞቹን በመቀነስ ያወጣ የነበረውን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማስቀረት አቅዷል
ቢቢሲ አንድ ሺህ ሰራተኞቹን ሊቀንስ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ከተመሰረተ 100 ዓመት የሞላው የእንግሊዙ ብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ቢቢሲ) በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ 1 ሺህ ሰራተኞችን የመቀነስ እቅድ እንዳለው አሳውቋል፡፡
ተቋሙ ቢቢሲ አራት እና ሲቢቢሲ የተሰኙ ቻናሎቹ ስርጭቶችን እንደሚያቆም አስታውቋል፡፡ ሲቢቢሲ ተቋሙ የህጻናት ፕሮግራሞችን የሚያስተላልፍበት ቻናል ነው፡፡
ቢቢሲ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የሀገሪቱ መንግስት የሚያደርግለትን የበጀት ድጎማ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንደሚያቋርጥ ማሳወቁን ተከትሎ እንደሆነ አልሮያ የጠተሰኘው የአረብ ኢምሬት ሚዲያ ዘግቧል፡፡
የመንግስትን ውሳኔ ተከትሎም ከዚህ በፊት ቢቢሲ ወርልድ ኒውስ እና ቢቢሲ ኒውስ ቻናል በሚል ለየብቻ ሲሰራጩ የነበሩ ሚዲያዎችን ባንድ ላይ በማድረግ በበይነ መረብ በመታገዝ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት መወሰኑም ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም ቢቢሲ ራዲዮ አራት በመባል ሲሰራጭ የነበረው የመደበኛ ስርጭት ቀርቶ በኢንተርኔት እንዲሰራጭ ተወስኗልም ተብሏል፡፡
የቢቢሲ ጠቅላላ ስራ አስኪያጅ ቲም ዴቪ አዲሱን ውሳኔ አስመልክቶ እንዳሉት ውሳኔው ጠንካራ የድጅታል ቢቢሲ ሚዲያ መመስረት አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡
ቢቢሲ 75 በመቶ ተከታዮቹን በአዲሱ ቢቢሲ አይፕሌየር በኩል የመድረስ እቅድ እንዳለውም አስታውቋል፡፡
ቢቢሲ አዲስ ባስቀመጠው የዲጂታል ስርጭት መሰረት በአንድ ዓመት ውስጥ 500 ሚሊዮን ፓውንድ ለማትረፍ ያሰበ ሲሆን በቀጣይም በዲጂታል መሰረተ ልማቶች ላይ ትኩረት ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት እና ዓለማችን ቢቢሲ ወደ ዲጂታል ስርጭቶች እንዲገቡ ይፈልጋሉ ያሉት ስራ አስኪያጁ ከዚህ በፊት ያልታዩ የዲጂታል ሚዲያ የስርጭት መንገዶችን እንደሚከተልም አክለዋል፡፡
በፈረንጆቹ 1922 የተመሰረተው ቢቢሲ እንግሊዝ በዓለም ላይ ለተጫወተችው ዓለም አቀፍ ፖለቲካ ትልቁን አስተዋጽዖ እንዳበረከተ ይገለጻል፡፡