ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያስገባው ኖሊውድ እንኳይ ይህን ያህል የሚዲያ ባለሙያዎች አልቀጠረም ተብሏል
በናይጀሪያ የአንድ ክልል አስተዳዳሪ 47 የሚዲያ አማካሪዎች መቅጠሩ አነጋጋሪ ሆኗል።
ፕሬዝዳንት ቲንቡ አዳዲስ የክልል አስተዳዳሪዎችን እየሾሙ ሲሆን አዳማዋ ለተሰኘችው ግዛትም አህመድ ፊንትሪን ሾመዋል።
ይህን ተከትሎም አዲሱ አስተዳዳሪ 47 የሚዲያ ቡድን አደራጅቻለሁ በማለቱ ናይጀሪያዊያን እያሾፉበት ይገኛሉ።
- ናይጀሪያ የዩንቨርሲቲ መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር ጾታዊ ግንኙት እንዳይጀምሩ የሚከለክል ህግ አወጣች
- ናይጀሪያ የእንግሊዘኛ ቋንቋ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳይሰጥ አገደች
አስተዳዳሪው በትዊተር ገጹ ላይ "47 አባላት ያሉት የሚዲያ ባለሙያ አዘጋጅቻለሁ" ማለቱን ተከትሎ ናይጀሪያዊያን የተለያዩ አስተያየቶችን በመስጠት ላይ ናቸው።
ለናይጀሪያ ቢሊዮኖች ዶላር ገቢ የሚያስገኘው ኖሊውድ እንኳን ያንተን ያህል የሚድያ ባለሙያዎች ቡድን አላዋቀረም እያሉት ይገኛሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሌሎች ደግሞ አስተዳዳሪው ግዛቲቱን ከማስተዳደር ይልቅ የሚዲያ ፕሮዳክሽን ኩባንያ በማቋቋም ላይ ሊሆን ይችላል ሲሉም ትችት ተሰንዝሮበታል።
በአዲሱ አስተዳዳሪ የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን ውስጥ 2 ልዩ የማህበራዊ ሚዲያ፣ 10 የሚዲያ ረዳቶች እና 35ቱ ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት አዘጋጆች እና ረዳቶች ናቸው ተብሏል።
አስተዳዳሪው ለምን ይህን ያህል የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲኖሩት ፈለገ? እሚለው ጉዳይ አሁንም አንጋጋሪነቱ የቀጠለ ሲሆን ሀላፊው በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
የፕሬዝዳንት ቲንቡ አስተዳድር የመንግሥትን ወጪ እንደሚቀንሱ ከዚህ በፊት መናገራቸው ይታወሳል።
ይሁንና የአንድ ግዛት አስተዳዳሪ 47 አባላት ያሉት የሚዲያ ቡድን እያዋቀረ የመንግስት ወጪን እንዴት መቀነስ ይቻላል? ሲሉ የሀገሪቱ ዜጎች ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።