በናይጀሪያ የአዲሱ ናይራ ኖት እጥረት ባንኮችን እስከማቃጠል የደረሰ ቁጣን አስነስቷል
አዳዲሶቹን ኖቶች ለመቀየር ረጃጅም ሰልፎችን ከመጠበቅ አልፈው በባንኮች አካባቢ የሚያድሩ ሰዎች እንዳሉም ተነግሯል
ከ10 ቀናት በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የምታካሂደው ናይጀሪያ፥ አዲሱን የናይራ ኖት ለመቀየር ያስቀመጠችውን ቀነ ገደብ እንደምታራዝም ይጠበቃል
በምዕራባ አፍሪካዊቷ ሀገር ናይጀሪያ አዲሱ የገንዝብ ኖት ቅየራ ነውጥ መፍጠሩ ተገለጸ።
አዳዲሶቹን የ200 ፣ 500 እና 1 ሺህ ናይራ ኖቶች ለመቀየር ናይጀሪያውያን ለሳምንታት ረጃጅም ሰልፎችን ይዘው ለመጠባበቅ ተገደዋል።
የአዳዲሶቹ ኖቶች እጥረትም በቤኒን እና ዋሪ ከተሞች ባንኮችን እስከማቃጠል የደረሰ ነውጥ ማስከተሉ ነው የተነገረው።
በበርካታ ከተሞችምአዳዲሶቹን የናይራ ኖቶች ለመቀየር በሌሊት ሰልፍ ለመያዝ የሚጓዙ እና በባንኮች አካባቢ የሚያድሩ ሰዎች እንዲበራከቱ እያደረገ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
የሰልፎቹ መርዘም ወደ ነውጥ ተቀይሮም የዝርፊያ ሙከራ የተደረገባቸው ባንኮች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ዘገባው አንስቷል።
በቤኒን ከተማ የሚገኘውን የናይጀሪያ ማዕከላዊ ባንክ ለመውረር የተደረገው ሙከራም በጸጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጭስ መቀልበሱ ነው የተገለጸው።
ናይጀሪያ በጥቅምት ወር 2022 ነበር አዳዲሶቹን የናይራ ኖቶች መቀየር የጀመረችው።
ይሁን እንጂ ከ40 በመቶ በላይ ህዝቧ ገንዘቡን በባንክ በማያስቀምጥባት ሀገር፥ አሁንም ድረስ አሮጌዎቹ የናይራ ኖቶች በስፋት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ቀጥለዋል።
አዳዲሶቹ የናይራ ኖቶች በበቂ ደረጃ አለመቅረባቸውም በኢባዳን ከተማ መንገድ የመዝጋትና ባንኮች ላይ ነውጥ የመፍጠር ሙከራ እንዲደረግ ምክንያት መሆኑን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችም ተለቀዋል።
ይህ ነውጥም ከ10 ቀናት በኋላ በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ኦል ፕሮግረሲቭስ ኮንግረንስ ፓርቲ ፈተና እንዳይሆንበት ተሰግቷል።
የናይጀሪያ ማዕከላዊ ባንክ የአዳዲሶቹ የናይራ ኖቶች ቅያሬ በፈረንጆቹ የካቲት 10 2023 እንደሚጠናቀቅ አሳውቆ የነበረ ቢሆንም፥ 10 ግዛቶች ባቀረቡት ቅሬታ አሮጌዎቹ ኖቶች አሁንም ድረስ ስራ ላይ ናቸው።
ምርጫው ከሚደረግበት ሶስት ቀናት በፊትም የናይራ ኖት ቅየራው እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
በበርካታ ከተሞች ረጃጅም ሰልፍ እና ነውጥ ያስከተለው ይሄው ጉዳይ የሰሞኑ አጀንዳ ሆኖ መቀጠሉም አይቀሬ ይመስላል።