ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ናይጄሪያዊያን የሀገሪቱን ኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ አገልግሎት አቋረጡ
በ10 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን ከሰኞ ጀምሮ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኙ አይደለም
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀጣጠለው የሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ ዝቅተኛ የደሞዎዝ ወለል እንዲስተካከል የሚጠይቅ ነው
በደምዎዝ ምክንያት ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ናይጄሪያዊያን የሀገሪቱን ኤሌክትሪክ ማሰራጫ አገልግሎት አቋረጡ።
ዝቅተኛ የደምዎዝ ወለል እንዲሻሻል በሀገር አቀፍ ደረጃ የስራ ማቆም አድማ ያደረጉ ናይጄሪያውያን ሀገሪቱን በጨለማ ውስጥ አሰንብተዋታል፡፡
ሰኞ እለት ወደ ሀገሪቱ ብሄራዊ የሀይል ማሰራጫ ያመራው የሰራተኞች ህብረቱ የሀገሪቱን የኤሌትሪክ ሀይል አቅርቦት አቋርጧል፡፡
ወደ ሀይል ማሰራጫ ጣብያው በጉልበት ሰብረው የገቡት ሰዎች በማሰራጫው ሰራተኞች ላይ አካላዊ ድብደባ መፈጸማቸው ተሰምቷል፡፡
በናይጄሪያ የሰራተኞች ኮንግረስ እና የንግድ ህብረት ኮንግረስ አስተባባሪነት የሚመራው አድማ ዝቅተኛ የደምዎዝ ወለልን ለማሻሻል ከመንግስት ጋር ሲደረጉ የነበሩ ድርድሮች ስኬታማ አለመሆናቸውን ተከትሎ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ነው፡፡
ሰራተኞቹ በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ተግባር ላይ ያለው 30 ሺህ ናይራ (የናይጄሪያ ገንዘብ) መነሻ ደምዎዝ ወደ 494ሺ ናይራ ወይም ወደ 369.6 ዶላር ከፍ እንዲል ጠይቀዋል፡፡
መንግስት በበኩሉ ቀድሞ የነበረውን የደምዎዝ ወለል በመቶ እጥፍ በመጨመር ከ60 ሺህ ናይራ በላይ መክፈል እንደማይችል አቋሙን አሳውቋል፡፡ የሰራተኛ ህብረቱ በሀገሪቱ የሚገኝውን የሸቀጦች ዋጋ ውድነት ለመቋቋም መንግስት አድርገዋለሁ ያለው ማሻሻያ በቂ ነው ብሎ አያምንም።
ይህን ተከትሎ ወደ አመጻ እና የስራ አድማ የገቡት ናይጄሪያዊያን ከሰኞ ጀምሮ የሀገሪቱ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጥ ፣አለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ በረራዎችም እንዲስተጓጎሉ አድርገዋል፡፡
ስራ ይበዛባቸዋል ከሚባሉት አቡጃ እና ሌጎስ አየር ማረፊያዎች የሚነሱ እና የሚያርፉ አውሮፕላኖች ባሉበት እንዲቆዩ ተደርጓል፡
ከዚህ ባለፈም ግዙፍ ሆስፒታሎች በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸው ተሰምቷል፡፡ በደቡብ ምእራብ ናይጄሪያ የሚገኙ ሆስፒታሎች ወሳኝ የሚባሉ የህክምና ቁሳቁሶቻቸው የሀይል እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡
የሀገሪቱ የፍትህ ሚንስትር ለሰራተኞች ህብረቱ በላከው ደብዳቤ ህገ ወጥ ያለውን አድማ ሰራተኞቹ እንዲያቆሙ፣ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ እና ከመንግስት ጋር ጉዳዩን በሰላም እንዲፈቱት ጠይቋል፡፡
ናይጄሪያውያን ዜጎች የሰራተኞቹን አድማ በሁለት ጽንፍ ተከፍለው እየተከራከሩበት ይገኛል፤ አንዳንዶቹ አድማው ትክክል መሆኑን፣ መንግስት ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎቹን እንዲፈትሽ ያደርጋል ሲሉ ሌሎች ደግሞ በሁኔታው በዙ ሰዎች እንደሚጎዱ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
ከፍተኛ የዋጋ ንረት በሚገኝባት ናይጄሪያ መንግስት የኑሮውን ጫና ለማርገብ ቤት ለቤት የምግብ ድጎማ ለማድረግ እቅድ አውጥቷል፡፡
ናይጄርያ ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት በ4ተኛ ደረጃ ብትገኝም በሀገሪቱ ተግባራዊ የሚደረገው የዝቅተኛ የደምዎዝ ወለል ከእርሷ በኢኮኖሚ ካነሱ ሀገራትም ጭምር ዝቅተኛ መሆኑን ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡