የቦኮ-ሀራም መሪ አቡበከር ሼካው መሞቱ እየተነገረ ነው
ዜናው እውነት ከሆነ በሽብር ተግባር በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን በተገደሉባት ናይጄሪያ ለውጥ እንደሚያመጣ ተገምቷል
ቦኮ-ሀራም ከባላንጣው ጂሃዲስት ቡድን ጋር በተደረገ ውግያ ወቅት ፣ አቡበከር ራሱን ማጥፋቱ ነው የተገለጸው
የቦኮ ሀራም መሪ አቡበከር ሸካው በምዕራብ አፍሪካ ከሚንቀሳቀሰው እና ባላንጣው ከሆነው የምዕራብ አፍሪካ ግዛት እስላማዊ መንግስት (Iswap) በማለት ራሱን ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር በተደረገ ጦርነት እንደሞተ ነው የፈረንሳዩ ዜና ወኪል/ኤ ኤፍ ፒ/ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
በሁለቱ ጽንፈኛ ቡድኖች መካከል በተደረገው ውጊያ ወቅት ፣ አቡበከር ሼካው ራሱን እንዳጠፋ የቦኮ ሀራም ተቀናቃኙ ቡድን አስታውቋል፡፡
የአይ.ኤስ.ዋፕ ((Iswap) መሪ አቡ ሙሳብ አል-ባራዊ “አቡበከር በመጨረሻው ዓለም ውርደትን ከመቀበል ይልቅ በምድር ላይ መዋረድን መርጧል ፤ ፈንጂ በማፈንዳት ወዲያውኑ ራሱን አጥፍቷል” ሲል በካኑሪ ቋንቋ ባሰራጨው የድምፅ መልዕክት ተናግሯል፡፡ ይሁንና ኤ.ኤፍ.ፒ እጄ ላይ ገብቷል ያለው የድምፅ መልእክት መቼ የተቀረፀ ነው ለሚለው ማረጋገጫ የለም፡፡
የተቀረፀው ድምፅ ከባድ የተኩስ ልውውጥ እንደነበረ እና ይህን ተከትሎ አቡበከር አፈግፍጎ ማምለጡን ፣ ለአምስት ቀናት በጫካ ውስጥ ሲንከራተት መቆየቱን እንዲሁም የአይ.ኤስ.ዋፕ ታጣቂዎች ያካሄዱትን መጠነ ሰፊ የማደን ስራም ያስረዳል፡፡
የአይ.ኤስ.ዋፕ ታጣቂዎች “አቡበከር እና የሚመራው ጦር ንስሀ እንዲገቡ እና አጅ እንዲሰጡ ቢጠየቁም እምቢ በማለት አቡበከር ራሱን አጥፍቷል” ይላል ተቀረጾ የተለቀቀው ድምጽ፡፡
ከዚህ ቀደምም አቡበከር ሼካው መሞቱ የተገለጸ ቢሆንም ፣ ከናይጄሪያ መንግስትም ይሁን ከቦኮ ሀራም ማረጋገጫ አልተሰጠም፡፡
የአቡበከር ህልፈት እውነት መሆኑ ከተረጋገጠ ፣ ላለፉት 12 ዓመታት ያክል በጂሃዲስቶች አመፅ ምክንያት ከ 40,000 በላይ ዜጎቿን ላጣችውና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ሚልዮኖች ለተፈናቀሉባት ናይጄሪያ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡
አይ.ኤስ.ዋፕ እ.ኤ.አ 2016 የቦኮ-ሀራም መሪ አቡበከር ሙስሊም ንፁሀንን ዒላማ ያደረገ አካሄድ ይከተላል በሚል ልዩነት ከቦኮ-ሀራም ተከፍሎ የወጣ አማፂ ክንፍ ነው፡፡