ንጉሡ ክልሉ ከ"ነዳጅ የዘለለ አማራጭ ማማተር ይጠበቅበታል" ሲሉም ተደምጠዋል
በናይጄሪያ በነዳጅ ሃብቷ በምትታወቀው ዴልታ ክልል አዲስ ንጉስ ተሰየሙ፡፡በዴልታ ግዛት በኢትስክሪ ሰዎች የተሰየሙት ንጉሥ ኦጂአም አቱዋቴ 3ኛ መሆናቸውም ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የንጉሱ መሾም ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ የናይጀርያ ወጣቶች እና የንጉሳውያን ቤተሰብ ወዳጆች ወደ ጎዳናዎች በመውጣት ደስታቸው በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ኡንቲኖሶትሶሶላ ኤሚኮ ተብሎ በሚታወቅ ስፍራ እንደተወለዱ የሚነገርላቸው የ37 ዓመቱ ንጉሥ ኦጂአም ፤በዎሪ ኦሉ ዙፋን ላይ የወጡ 21ኛው ንጉሥ ናቸው ተብሏል፡፡
የ37 ዓመቱ ንጉሥ ኦጂአም እስካሁን ከነገሱ በእድሜ ታናሽ ከሆኑ ንጉሦች አንዱ ናቸው፡፡
ንጉሡ በደጋፊዎቻቸው ፊት ያደረጉት ተስፋ የሚያሰንቅና በተራማጅ አመለካከት የታጀበ ንግግር፤ በሀገሪቱ የአመራር ውድቀት ሲያለቅሱ የቆዩትን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ያነቃቃ እንደነበርም ተገለጸዋል፡፡
ሰፋ ያሉ ጉዳዮች ባነሱበት ወቅት ንጉሡ፤ ክልሉ ከ"ነዳጅ የዘለለ አማራጭ ማማተር ይጠበቅበታል " ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ናይጀርያ በአፍሪካ ትልቋ የነዳጅ አምራች ሀገር ስትሆን ይህም ለሀገሪቱ አጠቃላይ የኤክስፖርት ገቢ 86 በመቶ አስተዋፅኦ እንዳለው ይታወቃል።
በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው የኒጀር ዴልታ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሰርጎ ገቦች የሚታመስ እና በተለያዩ የኃይል ኩባንያች ምክንያት ብክለት የሚስተዋልበት ክልል ሆኖ ቆይቷል፡፡
አዲሱ የክልል ንጉሥ ይህ እንዲስተካከል እንደሚሹ በንግግራቸው አመላክቷል፡፡
“ከነዳጅ ባሻገር መመልከት እና ጉልበታችንን በትክክለኛው አቅጣጫ ማሰራጨት አለብን”ም ነው ያሉት ንጉሡ። የንጉሱ ንግግር ወደ ተግባር እንዲለወጥ የበርካቶች ምኞት እንደሆንም ነው የሲኤንኤን ዘገባ ጠቅሷል፡፡