ጠ/ሚኒስትሩ፤ በናይጀሪያ ከህወሃት ሰዎች ጋር እንደተገናኙ ተደርጎ በተገለጸው ጉዳይ ላይ መንግስት ምላሽ ሰጠ
መንግስት፤ ህወሃት ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማጋጨት እየሰራ ነው ማለቱ ይታወሳል
ጠ/ሚኒስትሩ ከህወሃት ተወካዮች ጋር ተገናኝተዋል የሚሉ ዘገባዎች ሲወጡ ነበር
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በናይጀሪያ ከህወሃት ሰዎች ጋር እንደተገናኙ ተደርጎ በተሰራጨው መረጃ ዙሪያ ጽህፈት ቤታቸው ምላሽ ሰጠ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ናይጀሪያ የተጓዙት ከህወሃት ተወካዮች ጋር ለመነጋገር እንደሆነ ተደርጎ እየተሰራጨ ያለውን መረጃ ተከትሎ ለአል ዐይን አማርኛ ምላሽ ሰጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባሳለፍነው ሳምንት ናይጀሪያ ሲገቡ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሀመዱ ቡሀሪ አቀባበል እንደተደረገላቸው ጽህፈት ቤታቸው መግለጹ ይታወሳል። ፕሬዝዳንት ሞሀመዱ ቡሀሪ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አቀባበል ካደረጉ በኋላም የሁለትዮሽ ውይይት ተደርጓል።
ይሁንና ከ 90 ሺህ በላይ ተከታይ ያለውና የትዊተር ማረጋገጫ ምልክት የተሰጠው ጋሮ ኦንላይን የተባለ የትዊተር ገጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከህወሃት ተወካዮች ጋር በድብቅ መገናኘታቸውን ጽፏል።
ሌሎች ገጾች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና ከአሁኑ የህወሃት ተወካይ ብርሃኔ ገ/ክርስቶስ ጋር በናይጀሪያ በድብቅ እንደተገናኙ ሲዘግቡ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት እንደሻከረ በሽብር ለተፈረጀው ህወሃት ተወካዮች እንደገለጹላቸው ሲዘገብ ነበር።
አል ዐይን አማርኛ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ማብራሪያ ጠይቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም ለአል ዐይን አማርኛ በሰጡት ምላሽ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ናይጀሪ የሄዱት ከህወሃት ሰዎች ጋር ለመገናኘት እንደሆነ ተደርጎ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ውሸት መሆኑን ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የናይጀሪያ ጉብኝት ይፋዊ ጉብኝት መሆኑን የገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም፤ ከዚህ ውጭ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ናይጀሪ የሄዱት ከህወሃት ሰዎች ጋር ለመገናኘት እንደሆነ ተደርጎ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ ከቢለኔ ስዩም በተጨማሪም ሌላ በጉዞው የተሳተፉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል።
የኤርትራና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ግንኙነት በሚመለከት ትናንት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፤ ህወሃት ወደ ኤርትራ ትንኮሳ እያደረገ እንደሆነና ይህም ሁለቱን ሀገሮች ወደ ግጭት ለማስገባት እንደሆነ ተናግረው ነበር።
ሚኒስትሩ፤ በህወሃት ምክንያት ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ወደ ግጭት እንደማያመሩ ለአል ዐይን አማርኛ መግለጻቸው ይታወሳል።