ናይጄሪያ የጉዞ ክልከላ በጣሉባት 4 ሀገራት ላይ ተመሳሳይ እገዳ በመጣል መልስ ልሰጥ ነው አለች
አራቱ ሀገራት ከአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ‘ኦሚክሮን’ ጋር ተያይዞ ነበር በናይጄሪያ ላይ የጉዞ እገዳ የጣሉት
ናይጄሪያ የጉዞ እገዳውን በካናዳ፣ ብሪታኒያ፣ አርጀንቲናና ሳዑዲ አረቢያ ላይ ነው ለመጣል ያሰበችው
የናይጄሪያ መንግስት በሀገሪቱ ላይ የጉዞ እገዳ በጣሉ አራት ሀገራት ላይ ተመሳሳይ እገዳ በማጣል ምለሽ ለመስጠት ማሰቡን አስታወቀ።
ሀገሪቱ ከነገ ማክሰኞ ጀምሮ ከካናዳ፣ ብሪታኒያ፣ አርጀንቲና እና ሳዑዲ አረቢያ የሚነሱ መንገደኞች ወደ ናይጄሪያ እንዳይገቡ ለመከልከል ማቀዷም አስታውቃለች።
- ፕሬዚዳንት ራማፎሳ በደቡብ አፍሪካ ላይ እየተጣለ ባለው የጉዞ እገዳ “በጣም ተበሳጭቻለሁ” አሉ
- ጉቴሬዝ ከ‘ኦሚክሮን’ጋር በተያያዘ የተጣሉ የጉዞ እገዳዎችን ‘አፓርታይድ’ ሲሉ ኮነኑ
ናይጄሪያ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰቸው አራቱም ሀገራት ከአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ‘ኦሚክሮን’ ጋር ተያይዞ ከሀገሪቱ የሚነሱ መንገደኞች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ ክልከላ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
የናይጄሪያ አቪዬሽን ሚኒስትር ደኤታ ሃዲ ሲሪካ በኢኮኖሚ ማእከል በሆነች ሌጎስ ከተማ በሰጡት መግለጫ፤ የሀገሪቱ መንግስት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከናይጄሪያ የሚነሱ ዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ ለተጣለው እገዳ ምላሽ ለመስጠት ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ደኤታው አክለውም፤ ናይጄሪያን በቀይ መዝገባቸው ውስጥ ያስቀመጡ ሀገራት አየር መንገዶቻቸው ወደ ናይጄሪያ ለንግድ እንዲበሩ ለማድረግ የሞራል መብት እንደሌላቸውም ተናግረዋል።
“እኛ የምናደርገው እነሱ ያደረጉብንን ነው፤ የኛ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ የሚከለክሉ ከሆነ የእነሱ ዜጎችም ወደ ሀገራችን አይገቡም” ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፤ “ዛሬ ወይም ነገ እነዚህ ሀገራት በናይጄሪያ የኮሮና ቫይረስ ቀይ መዝገብ ላይ እንደሚሰፍሩም እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።
“ኦሚክሮን” የሚል መጠሪያ የተሰጠው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንደተገኘ መነገሩ ይታወሳል።
አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በአሁኑ ወቅት በበርካታ የዓለም ሀገራት ውስጥ የተገኘ ሲሆን፤ በአፍሪካም እስካሁን በ11 ሀገራት ውስጥ መገኘቱን ሲዲሲ አፍሪካ አስታውቋል።
የናይጄሪያ መንግስትም ከሌሎች ሀገራት ወደ ሀገሪቱ የገቡ ስድስት ሰዎች ላይ አዲሱን የኮሮና ቫይረስ ዝርያ “ኦሚክሮን” መገኘቱን አስታውቋል።