ናይጄሪያ ከመንግስት የባንክ ሂሳቦች ገንዘብ ማውጣትን ልትከለክል ነው
አዲሱ ህግ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና ሙስናን ለመዋጋት ያለመ መሆኑ ተገልጿል
የመንግስት ባለስልጣን ገንዘብ ማውጣት ሲፈልጉ ለፕሬዝዳንቱ ማመልከት አለባቸው ተብሏል።
ናይጄሪያ ከመንግስት የባንክ ሂሳቦች ገንዘብ ማውጣትን ልትከለክል ነው።
የናይጄሪያ የፋይናንስ ደህንነት ክፍል የሀገሪቱ ባለስልጣናት ከፈረንጆቹ መጋቢት ጀምሮ ከመንግስት ሂሳቦች ገንዘብ እንዳያወጡ መከልከሉን በመግለጫው ተናግሯል።
የፌዴራል፣ የአከባቢ እና የክልል ባለስልጣናት ላይ ተፈጻሚ ይሆናል የተባለው አዲሱ ህግ፤ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና ሙስናን ለመዋጋት ያለመ ነው ተብሏል።
በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ቀዳሚ የሆነችው ሀገር እርምጃው ወደ ወረቀት-አልባ ገንዘብ ምጣኔ-ሀብት ለመሸጋገር መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጋር የሚስማማ መሆኑ ተነግሯል።
የሀገሪቱ የፋይናንስ ደህንነት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሞዲቦ አር ሃማን ቱኩር በመግለጫው ላይ "የመንግስት ሰራተኞች ለማጭበርበርና ለወንጀሎች የበለጠ ተጋላጭ እየሆኑ ነው" ብለዋል።
ተቋሙ እንዳመለከተው ከፈረንጆቹ 2015 እስከ 2022 ባለስልጣናት ሁለት ነጥብ አራት አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከመንግስት ሂሳቦች አውጥተዋል። ይህም አብዛኛው ቀድሞ ከነበረ የማውጣት ገደቦች ያለፈ ነው መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ኃላፊው በመግለጫቸው አንድ የመንግስት ባለስልጣን ገንዘብ ማውጣት ሲፈልግ ለፕሬዝዳንቱ እንዲፈቀድለት ማመልከት ይችላል ብለዋል።
የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመግታት እና ወደ ወረቀት-አልባ ምጣኔ-ሀብት ለመሸጋገር የወጪ ገደብ ማውጣትና አዲስ የተነደፉ የ200፣ 500 እና 1,000 ናኢራ ማሰራጨት ጀምሯል።
ከሰባት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ጥሬ ገንዘብ 85 በመቶው የሚሆነው ከባንክ ውጭ ነው ተብሏል።