ከ50 አመታት በላይ በበጎፈቃድ መቃብር የሚቆፍረው የናይጀሪያ ቤተሰብ
የወላጆቻቸውን አደራ የተቀበሉ ወንድማማቾች ያለመደበኛ ክፍያ አድካሚውን ስራ መከወናቸውን ቀጥለዋል
በጎፈቃደኞቹ "ወላጆቻችን ፈጣሪን ከሚያስደስተው ስራ በሰማይ ዋጋ ታገኙበታላችሁ" እያሉ አሳድገውናል ይላሉ
በናይጀሪያ ሰሜናዊ ክፍል ካዱና ከተማ አንድ ቤተሰብ ከ50 አመታት በላይ ከባድ ሃላፊነት ተቀብሎ እየሰራ ነው፤ የሞቱ ሰዎችን ገንዞ፣ መቃብራቸውን ቆፍሮ መቅበር።
አድካሚው ተግባር በከተማዋ ነዋሪዎች ቤተሰቡን ታዋቂና ተመስጋኝ ያድርግ እንጂ እንደ ስራ ከታየ ክፍያ የለውም ማለት ያስደፍራል።
የአብዱላሂ ቤተሰብ ሰዎችን በመቅበር ተግባር የተሰማራው በ1970ዎቹ ነው። ኢብራሂም እና አዳሙ የተባሉ ወንድማማቾ የጀመሩት በጎ ስራ በልጆቻቸው ቀጥሎ አሁንም ድረስ ዘልቋል።
"ወላጆቻችን ፈጣሪ ይህን አገልግሎት እንደሚወደውና በአለማዊው ህይወት ክፍያ ባይኖረውም በሰማይ ግን ዋጋው ከፍ ያለ መሆኑን እየነገሩ ነው ያሳደጉን" ይላል የኢብራሂም አቡድላሂ ትልቅ ልጅ ማጋጂ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ።
ማጋጂ በአሁኑ ወቅት እድሜው 58 የደረሰ ሲሆን በቱዳን ዋዳ የመቃብር ስፍራ 18 በጎፈቃደኛ ቤተሰቦቹን አስተባብሮ የሞቱ ሰዎችን አፈር ያለብሳል።
ሶስት የአጎቶቹ ልጆችም በቀን ለ12 ስአት በሳምንት ለሰባት ቀናት ሟቾችን ገንዘው ለመቅበር ዝግጁ ሆነው ይጠባበቃሉ።
በካዱና የማጋጂ ስልክ የሌለው የለም ማለት ይቻላል፤ የሞተ ሰው ሲኖር በቅድሚያ የሚደወለው ወደሱ ነው።
የስልክ ጥሪው እንደደረሰው ከበጎፈቃደኞቹ ውስጥ አንዱ ወደሟች ቤት ያመራና አስከሬን አጥቦ በጨርቅ ይጠቀልላል። የሟቹን ቁመት ለክቶ በመቃብር ስፍራ ለሚገኙት በመደወል በልኩ እንዲቆፈር ያደርጋል።
ሁለት መቃብር ቆፋሪዎች የካዱናን ከባድ ሙቀት ተቋቁመው መቃብር ለመቆፈር በጥቂቱ አንድ ስአት ይወስድባቸዋል።
"ዛሬ ብቻ ስምንት መቃብር ቆፍረናል፤ አንዳንድ ቀናት ከባድ ናቸው" የሚለው ማጋጂ፥ በከተማዋ የሃይማኖት ግጭት ሲከሰት እጅግ ፈታኝ ጊዜ እንደሚያሳልፉ ተናግሯል።
የቀብር ስርአቱ ተጠናቆ ሀዘንተኞች ወደቤታቸው ሲመለሱ የመቃብር ጠባቂው ላብ መተኪያ ይጠይቃሉ።
ይህን ተግባር ሁልጊዜም የሚፈጽሙት የ72 አመቱ ኢኑዋ ሞሀመድ ናቸው። አዛውንቱ የአብዱላሂ ቤተሰቦች ለማህበረሰቡ ያላቸውን ጉልህ ሚና ጠቅሰው የሟቾ ቤተሰቦች ያላቸውን እንዲደጉሟቸው ሃሳብ ያቀርባሉ።
ከሀዘንተኞች የሚገኘው ገንዘብ ለበጎፈቃደኞቹ የምሳ ወጪያቸውን ከመሸፈን አያልፍም፤ ኑሯቸውን የሚደጉሙት ከወላጆቻቸው በወረሱት አነስተኛ የእርሻ ማሳ ሰብል በማምረት ነው።
በቅርቡ ግን ድካማቸውን የተረዱት የከተማዋ አስተዳዳሪ ቋሚ ወርሃዊ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ወስነዋል።
አምስቱ ትልልቅ የአብዱላሂ ቤተሰቦች በወር 43 ሺህ ናይራ (28 ዶላር)፣ ወጣቶቹ ደግሞ 13 ዶላር ይከፈላቸዋል።
ደመወዙ ከናይጀሪያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል (45 ዶላር) ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም በጎፈቃደኞቹ በተለያዩ ችግሮች ተማረው ከመልካም ስራቸው እንዳይወጡ ሊያግዝ እንደሚችል ተገልጿል።