አሜሪካ በካቡል በፈጸመችው የአየር ጥቃት 9 የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገደሉ
በአሜሪካው የድሮን ጥቃት ከተገደሉት መካከል ስድስቱ ህፃናት መሆናቸውን ገልጸዋል
ጥቃቱ የተሰነዘረው በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ነው
አሜሪካ አሸባሪ ለመምታት ኢላማ አድርጓል ባለችው የአየር ላይ ጥቃት ዘጠኝ የአንድ ቤተሰብ አባላትን መግደሏ ተገለጸ።
ጥቃቱ የተሰነዘረው በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ እንደሆነ ተገልጿል።
ሲኤንኤን እንዳለው ዋሸንግተን፤ የቦንብ ጥቃት አድራሽ ነው በሚል የጠረጠረችውን ግለሰብ ለማጥቃት በሚል በወሰደችው ጥቃት ነው የአንድ ቤተሰብ አባላት የተገደሉት። ሲኤንኤን መረጃውን ከሟች ቤተሰቦች ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን ከሟቾች መካከል አንዲት ህፃን አለችበት ተብሏል።
የሟች ቤተሰቦች እና የአይን እማኞች “በካቡል የተገደሉት የቤተሰብ አባላት እንጅ አሸባሪዎች አይደሉም፤ እኛ አይ ኤስ አይደለንም” ማለታቸውንም ሲኤንኤን ዘግቧል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሟች ጎረቤቶች፤ በአሜሪካው የድሮን ጥቃት ከተገደሉት መካከል ስድስቱ ህፃናት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሟቾቹ ጎረቤቶች፤ እሳቱን ለማጥፋት ሲሮጡ እንደነበር ገልጸው ሲድስት ሰዎች መሞታቸውን ተመልክቻለሁ ብለዋል።
በዚህ ጥቃት ከሞቱት ግለሰቦች በተጨማሪም የተጎዱ ስለመኖራቸውም የአይን እማኞች ተናግረዋል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ ሽብርተኛ የተባለ ግለሰብን ለመግደል ዋሸንግተን፤ በካቡል የድሮን ጥቃት መፈጸሟን አስታውቋል።
ኮማንዱ በንጹሃኑ ላይ ጥቃት መድረሱን ገልጾ አንድ ተሽከርካሪ ሲወድም የሱ ፍንጥርጣሪ ጉዳት እንዳደረሰ ገልጿል፡፡ የኮማንዱ ቃል አቀባይ ካፒቴን ቢል አርባን ምን እንደተከሰተ እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል።