አምባሳደር ስለሺ በቀለ፤ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጋር በድርድርና በአጎአ ዙሪያ መወያየታቸው ተገለፀ
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ ስላለው የሰላም ውይይት ዙሪያ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል
ልዩ መልዕክተኛ በዚህ ሳምንት ወደ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ እንደሚመጡ ይጠበቃል
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በአፍሪካ ቀንድ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሚካኤል ሃመር ጋር መነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
አምባሳደር ስለሺ እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በተጀመረው ጥረትና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ነው ውይይት ማድረጋቸው የተገለጸው።
ሁለቱ ዲፕሎማቶች ስለመንግስትና ህወሃት ድርድር፤ ስለሰብዓዊ ድጋፍ፣ ብሔራዊ ምክክር፣ የሕዳሴ ድርድር፣ አጉዋ እንዲሁም ኤአር 6600 እና S3199 መወያየታቸው ተገልጿል፡፡
አምባሳደር ስለሺ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ያልተቆጠበ ስራ እየሰራ መሆኑን ለዲፕሎማቱ መናገራቸው ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ መንግስት በሀገሪቱ ሰላም ይመጣ ዘንድ የሥራ ሂደቶችን የጀመረ መሆኑን የገለጹት ዲፕሎማቱ፤ ይህንን ዕውን ለማድረግ ግን ሌኛው ወገንም ሊሰራ እንደሚገባ ነው ያነሱት።
በሌላኛው ወገን ያለው አካል ሰላም እንዲመጣ ቢሰራ መንግስት የጀመረው የሰላም ጥረት ዕውን እንደሚሆንም ነው የኢትዮጵያ ዲፕሎማት የገለጹት።
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሚካኤል ሃመር በበኩላቸው የተጀመረው የሰላም ጥረት እንዲሳካ ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
የአሜሪካ ዲፕሎማት ኢትዮጵያውያን ሰላም እንዲያገኙ ሀገራቸው ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቷንም ለአምባሳደር ስለሺ ገልጸዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
አምባሳደር ስለሺ መንግስት በግጭት እና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ የማድረሱ ስራ ያለእንቅፋት መቀጠሉን ማንሳታቸው ተገልጿል።
አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰዳቸው ላላቸው ጥረቶች አድናቆት እንዳለው መግለጹን የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
የሕዳሴ ግድብን በሚመለከት ኢትዮጵያ የምትከተለው አቋም ሚዛናዊ መሆኑን የገለጹ ሲሆን አምባሳደር ሚካኤል ሃመር ደግሞ ሶስቱ ሀገሮች ሁሉንም ጠቃሚ የሚያደርግ መንገድ ላይ ይደርሳሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
አምባሳደር ስለሺ ኢትዮጵያ ከአግዋ ተጠቃሚነቷ የወጣችበት መንገድና ማዕቀብ ለመጣል የተዘጋጁት ኤአር 6600 እና S3199 ረቂቆችም ረጅም ጊዜ ላስቆጠረው የአዲስ አበባንና የዋሸንግተንን ግንኙነት የሚመጥን እንዳልሆነና መስተካከል እንዳለበት መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወደ አጉዋ ተጠቃሚነት እንዲትመለስ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው ጠቃሚ መሆኑን መግለጻቸውን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የገለጸው።
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሚካኤል ሃመር በዚህ ሳምንት ወደ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ እንደሚመጡ ይጠበቃል።