ኢራን በ2015 ከተነሱት ነጥቦች ውጭ ጥያቄዎች ውጭ ሌላ ፍላጎት የለኝም ብላለች
አሜሪካ እና ኢራን እ.አ.አ በ2015 በተፈረመው የኒውክለር ስምምነት ላይ መደበኛ ያልሆነ ንግግር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዋሸንግተን እና ቴህራን ባደረጉት ውይይት ኢራን የኒውክለር ስምምነቱን እንደገና ለማስጀመር አዲስ ቅድመ ሁኔታ እንዳላስቀመጠች ገልጻለች፡፡ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቴህራን የኒውክለር ስምምነቱን ለመመለስ የምታስቀምጠው አዲስ ቅድመ ሁኔታ እንደሌለ ይፋ አድርጓል፡፡
አሜሪካ፤ ኢራን ከ 2015 ቱ ስምምነት ጋር የማይገናኝ አዲስ ቅድመ ሁኔታ እንዳስቀመጠች ገልጻ ነበር፡፡ ኢራን ደግሞ ይህንን አሜሪካን ክስ እንደማትቀበለውና አዲስ ጥያቄዎች እንደሌሏት አሳውቃለች፡፡
የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አሚር አብዱላሂ ከኳታሩ አቻቸው ጋር በዶሃ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ከ2015 የኒውክለር ስምምነት ውጭ ያለ አዲስ ጥያቄ እንደሌለ አንስተዋል፡፡ ፡ የቴህራን ጥያቄዎችና ፍላጎቶች በሙሉ በ2015 የተቀመጡ እንደሆኑም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት፡፡
ስምንተኛው የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራዒሲ፤ በቀድሞው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሰረዘው የ2015 የኒውክለር ስምምነት እንዲመለስ ጥረት እንደሚያደርጉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አሜሪካን እና ቀሪዎቹን አምስት ምዕራዊ ሃገራት ወደ ስምምነቱ ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርጉም ነበር ለኢራናውያን ቃል የገቡት፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ተግባርም በአሜሪካ ተጣሉትን ማዕቀቦች እንዲነሱ ጥረት እንደሚያደርጉና የተከፉ ኢራናውያንን እንደሚክሱ ይፋ አድርገው ነበር፡፡
ይህንን ተከትሎም አሜሪካ እና ኢራን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስለስምምነቱ መነጋገራቸው ተሰምቷል፡፡
የ2015 ቱ ስምምነት ኢራን የኒውክለር መርሃ ግብሯን ለማስቀጠል የምታበለጽገውን ዩራኒዬም መጠን እንድትቀንስ በምላሹም የተጣሉባት የጋራና የተናጠል ማዕቀቦች እንዲነሱ የሚደነግግ ነበር፡፡
በኢራን በኩል ስምምነቱን ፈርመው የነበሩት በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ ነበሩ፡፡
ሆኖም ስምምነቱ የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፋ ነው ሲሉ የስምምነቱን ፈራሚ የፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የአስተዳደር አካላትን የተቹት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸውን ከስምምነቱ ማስወጣታቸው ይታወሳል፡፡
አሁን በሩሲያ - ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለከፍተኛ የነዳጅ ፍላጎት ክፍተት የተዳረገችው አሜሪካ ግን ወደ ስምምነቱ የመመለስና የኢራን ነዳጅ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርብበትን መደላድል የመፍጠር ፍላጎት እንዳላት ተሰምቷል፡፡