የቬኔዙዌላ እና የኢራን ነዳጅ ለዓለም አቀፍ ገበያ መቅረብ እንዲጀምር ጥሪ ቀረበ
ልዑኩ በሁለትዮሽ እና በታሰሩ አሜሪካውያን ጉዳይ ይመክራል ቢባልም የነዳጅ ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል
የአሜሪካ ተደራዳሪ ልዑክ ቬንዙዌላ ገብቷል
ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተተ የአሜሪካ ተደራዳሪ ልዑክ ቬንዙዌላ ገባ።
ልዑኩ ካራካስ የገባው ለዓመታት ሻክሮ የዘለቀው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻሻል በሚችልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ነው ተብሏል።
በቬኔዙዌላ የታሰሩ አሜሪካውያን ጉዳይ ከመነጋገሪያ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ተነግሯል።
የልዑኩን ካራካስ መድረስ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በቀጥታ የቴሌቪዥን ንግግራቸው አረጋግጠዋል። ከታማኝ የፓርቲያቸው ባለስልጣናት ጋር በመሆን ልዑካኑን እንደሚያገኙም ነው ማዱሮ የተናገሩት።
በቬኔዙዌላ ላይ ዘርፈ ብዙ ማዕቀቦችን የጣለችው አሜሪካ ከፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ መንግስት ጋር የከረረ ቅራኔ ውስጥ መሆኗ ይታወቃል።
ከማዱሮ ይልቅ ለተቃዋሚው ጁዋን ጓይዶ ሙሉ ድጋፍ እንዳላት ገልጻለች።
ካራካስ የገባው የአሜሪካ ልዑክም ቅራኔው ሊረግብና የሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ሊሻሻል በሚችልበት ሁኔታ ላይ ሊመክር እንደሚችል ይጠበቃል። በተለይ የነዳጅ ዋጋ እየናረ መምጣቱን ተከትሎ በቬንዙዌላ ነዳጅ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ጉዳይ የንግግሩ ዋና አጀንዳ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተነግሯል።
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የሩሲያን ነዳጅ ላለመግዛት የወሰኑት አሜሪካን መሠል ምዕራባዊ ሃገራት የነዳጅ ፍላጎታቸውን የሚሞላ አማራጭ ገበያን እያማተሩ ነው። ለዚህም ቬንዙዌላ እና ኢራን ዐይን ማረፊያዎቻቸው ናቸው።
ፈረንሳይ እንኳን ዛሬ የኢራን እና የቬኔዙዌላ ነዳጅ ለዓለም ገበያ መቅረብ እንዲጀምር ጥሪ አቅርባለች።
ይህ ግን ሃገራቱ በዘርፈ ብዙ ማዕቀቦች እንዲዳከሙና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገለሉ መደረጉን ተከትሎ በቀላሉ የሚሆን አይመስልም። ሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን እንደሚፈልግም የልዑካኑን ጉዞ አስመልክቶ የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።