የሰሜን ኮሪያው መሪ የሴት ልጄን ስም ማንም ሊጋራት አይችልም ማለታቸው ተነገረ
በኪም ልጅ ስም (“ጁ ኤ” ) የሚጠሩ ሴቶችም ስማቸውን እንዲቀይሩ እየተገደዱ መሆኑ ተገልጿል
ፒዮንግያንግ የፍቅር ስሞች "ቦምቡ፣ ሽጉጤ" እና መሰል ወታደራዊ ስሜት ባላቸው ስሞች እንዲቀየሩ ማዘዟም ይታወሳል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሴት ልጅ ስምን ሌሎች ሴቶች መጠቀም አይችሉም መባሉ ተገልጿል።
የአሜሪካው ራዲዮ ፍሪ ኤዥያ ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው፥ የኪም ጆንግ ኡን ልጅ ስም (“ጁ ኤ”) የሚጠሩ ሴቶች ስማቸውን በአፋጣኝ እንዲቀይሩ ታዘዋል።
በሰሜን ፒዮንጋን እና በደቡብ ፒዮንጋን ግዛቶችም ይሄው መመሪያ መተላለፉን ነው ዘገባው የተቀሰው።
- ሰሜን ኮሪያ የኪም ጆንግ ኡን ሴት ልጅ የሚያሳዩ አዳዲስ ቴምብሮች ይፋ ልታደርግ ነው
- ሰሜን ኮሪያውያን ለልጆቻቸው "ቦምቡ፣ ሽጉጤ" እና መሰል ሰሞችን እንዲያወጡላቸው አዘዘች
ዠንግዙ በተሰኘች ከተማም መሰል ስሞች ያሏቸው ሁለት ታዳጊዎች የልደት ካርዳቸው ላይ ያለውን ስማቸውን ይቀይሩ ዘንድ ለወላጆቻቸው ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት እንደደረሳቸው ሬዲዮ ፍሪ ኤዥያ ዘግቧል።
የኪም ልጅ ስም “ከፍተኛ ክብር” ለሚሰጠው ሰው የሚሰጥ መጠሪያ መሆኑንም ባለስልጣናቱ በምክንያትነት እንደሚጠቅሱ ነው ዘገባው የሚጠቁመው።
ፒዮንግያንግ ግን ለዚህ ዘገባ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠችም።
የ10 አመቷ ኪም ጁ ኤ ከኪም ጆንግ ኡን ሶስት ሴት ልጆች አንዷ ናት።
ከሁለት እህቶቿ በተለይ ከአባቷ ጋር በአደባባይ ደጋግማ የመታየቷ ነገርም የኪም ጆንግ ኡን በትረስልጣን ተረካቢዋ እሷ ሳትሆን እንደማትቀር ጥርጣሬውን አጉልቶታል።
ወጣቱ መሪ በሚሳኤል ማስወጨፊያ ጣቢያዎች ጭምር ጁ ኤን እጇን ይዘው መገኘታቸው የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት መሳቡ አይዘነጋም።
ፒዮንግያንግ የወታደራዊ ጦሯን 75ኛ አመት ምስረታ በግዙፍ ወታደራዊ ትርኢት ስታከብርም የ10 አመቷ ታዳጊ ከአባቷና ከፍተኛ ባለስልጣናት ጎን ነበረች።
ኪም ጆንግ ኡን ልጃቸውን ከወዲሁ ለስልጣን እያለማመዷት ነው ለሚለው መረጃ ቁብ የሰጡት አይመስልም።
ይልቁንም በፈረንጆቹ 2014 ያሳለፉትን ውሳኔ ደግመውታል፤ “ጆንግ ኡን” የሚል መጠሪያ ያላቸው ሞክሼዎቻቸው ስም እንዲቀይሩ እንዳደረጉት ሁሉ በ“ጁ ኤ” የምትጠራው ሴት ልጄ ብቻ ናት ብለዋል ይላል በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት ሬዲዮ ፍሪ ኤዥያ።
የሰሜን ኮሪያው መሪም ሆኑ መገናኛ ብዙሃን ግን በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጠዋል።
ፒዮንግያንግ ከዚህ ቀደምም የፍቅር ስሞች ጦር ጦር በሚሸቱ ስሞች እንዲቀየሩ ማሳሰቧ የሚታወስ ነው።
ተወዳጅ የሆኑ የፍቅር ስሞች የምዕራባውያን ባህል ያንጸባርቃሉ በሚል ነው የስም ቅያሬ ውሳኔው መተላለፉ የተነገረው።
የሰሜን ኮሪያን ርዕዮተ አለማዊ አስተሳሰብና ወታደራዊ ዝግጁነት ያሳያሉ የተባሉት አዳዲስ ስሞችም ቹንግ ኢ (ሽጉጤ እንደማለት)፣ ፖክ ኢ (ቦምቡ ወይም ቦምቢት)፣ ኡይ ሶንግ (ሳተላይት)፣ ቹንግ ሲም (ታማኝ) እና የመሳሰሉ ናቸው።
እነዚህ ስሞች የፒዮንግያንግን ርዕዮተ አለማዊ አስተሳሰብና ወታደራዊ ዝግጁነት እንደሚያሳዩም ታምኖባቸዋል።