በቻይና 132 ሰዎችን አሳፍሮ ከተከሰከሰው አውሮፕላን በህይወት የተረፉ ሰዎች ምልክት አልተገኘም
የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ አንድ ቡድን አውሮፕላኑ ወደ ተከሰከሰበት ቦታ መላኩን አስታውቋል
አውሮፕላኑ ከ31 ሺህ ጫማ ተምዘግዝጎ እንዲከሰከስ ያደረገው ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ነው
132 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737-800 በሀገር ውስጥ በረራ ላይ ሳለ በደቡባዊ ቻይና ግዛት በሚገኝ ተራራማ አካባቢ በትናትናው እለት ተከስክሷል።
እንደመገናኛ ብዙሃኑ ዘገባ ከሆነ በህይወት የተረፉ ሰዎች ምልክት አልተገኘም።
የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ከመግለጽ የተቆጠበው አየርመንገዱ ህይወታቸው ላለፈው መንገደኞች እና የበረራ ቡድን አባላት ሀዘኑን መግለጹን ፎይተርስ ዘግቧል።
አውሮፕላኑ የመከስከስ አደጋ የደረሰበት ከዩናን ግዛት ዋና ከተማ ወደ ወደ ጓንግ ዶንግ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ጉዋንዙ በመጓዝ ላይ ሳለ ነበር።
የቻይናው ኢስተርን አየርመንገድ እንደገለጸው አውሮፕላኑ ከ31 ሺህ ጫማ ተምዘግዝጎ እንዲከሰከስ ያደረገው ምክንያት በምርመራ ላይ ነው ተብሏል። ሮይተርስ የቻይናን ሚዲያ ጠቅሶ እንደዘገበው በበራራው ላይ የውጭ ሀገር ዜጋ የለም፡፡
አየርመንገዱ ለተሳፋሪዎቹ ዘመዶች ያሳወቀ ሲሆን፤ አንድ የምርመራ ቡድንም ወደ ቦታ መላኩን አስታውቋል።
በተጨማሪም የአሜሪካው የአውሮፕላን አምራች ቦይንግ ለቻይና ኢስተርን አየር መንገድ ሙሉ ድጋፋ እደሚሰጥ ያስታወቀ ሲሆን፤የአሜሪካው የፌደራል አቪዬሽን ባለስልጣንም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብሏል።
ከትናትናው ጉዋንዡ የአውሮፕላን አደጋ ቀደም ብሎ በቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ታሪክ 22 አደጋዎች ያጋጠሙ ሲሆን፤ ከኢነዚህም ውስጥ 10 አደጋዎች የበርካቶችን ህይወት የቀጠፉ ናቸው።
ከ22ቱ አደጋዎች ውስጥ የመጀመሪያው የቦይንግ 737-800 አውሮፕላን አደጋ በፈረንጀቹ በ2006 በብራዚል ያጋጠመ ሲሆን፤ በአደጋውም 154 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
የቅርቡ የቦይንግ 737-800 አውሮፕላን አደጋ ደግሞ በህንድ ያጋጠመ ሲሆን፤ በአደጋውም 21 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
የቦይንግ ምርት የሆነው 737-Max አውሮፕላንም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እና በኢንጆኔዥያ መከስከሱን ተከትሎ አውሮፕላኑ መራራ አቁሞ እንደነበረ ይታወሳል።