የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሜር ዘለንስኪ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት አግኘትዋል
የ2023 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በዛሬው እለት በኖርዌይ ኦስሎ በሚካሄድ ስነ-ስርዓት ከሰዓታት በኋላ ይፋ ይደረጋል።
ሰላምን በማምጣት እና ስለ ሰላም ለሰሩ ግለሰቦች አሊያም ተቋማት ለሚሰጠው የኖቤል የሰላም ሽልማት ዘንድሮ ከ350 በላይ ግለሰቦች እና ተቋማት በእጩነት ቀርበዋል።
የዘንድሮ የኖቤል የሰላም ሽላምት እጩዎች ብዛት 351 ሲሆን፤ ይህም በሽልማት ታሪክ ሁለተኛው ከፍተኛ ቁጥር ነው ተብሏል፤ በ2016 በተካሄደው የሽልማት ስነስርዓት ላይ 376 እጩዎች የቀረቡበት በታሪክ ከፍተኛው ነው።
ለዘንድሮ የኖቤል የሰላም ሽልማት በእጩነት ከቀረቡ መካከል 259 ግለሰቦች ሲሆኑ፣ 92 ደግሞ ተቋማት መሆናቸውም ነው የተገለጸው።
ለኖቤል የሰላም ሽልማት ከሩሲያ ጋር ጦርነት የገጠሙት የዩክሬኑ ፕሬዝዳት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በእጩነት የቀረቡ ሲሆን፤ ከፍተኛውን የአሸናፊነት ግምትም አግኝተዋል።
የሩሲያ መንግስት ተቀናቃኝ አሌክሲ ኔቫሊን የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸንፋሉ ተብለው ከሚጠበቁት መሀል ናቸው።
ባለሞያዎች የሴቶች፣ የነባር ሰዎችና የአካባቢ ተሟጋቾች ሽልማቱን በእጃቸው ሊያስገቡ ይችላሉ ብለዋል።
በኢራን በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙት፣ የሴቶች መብት ተሟጋች እና የሞት ቅጣትን የሚቃወሙት ናርጅስ መሀመዲ ሽልማቱን ሊወስዱ እንደሚችሉም ተጠብቀዋል።
አፍጋኒስታናዊው ማህቡባ ሴራጅ የሴት ልጆች የትምህርት መብት እና ሌሎች የሴቶች መብቶች እንዲከበር በመስራት የኖቤል ሽልማትን በእጃቸው ሊያደርጉ ይችላሉም ተብሏል።
ሆኖም ግን በግመታ የሚታወቁ ሰዎች የ2023ን የኖቤል የሰላም ሽልማት የዩክሬኑ ዘለንስኪ ለመውሰድ ቀዳሚ ናቸው እያሉ ነው።
በዛሬው እለት አሸናፊው ይፋ የሚደረግለት የኖርዌይ የኖቤል የሰላም ሽልማት፤ እንደከዚህ ቀደሙ አሸናፊው ከተጠበቀው ውጭ ሊሆን ይችላል ተብሏል።