ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከሶስት ዓመት በፊት ሽልማቱን ማሸነፋቸው ይታወሳል
የዘንድሮው የሰላም ኖቤል ሽልማት አንድ ሰው እና ሁለት ተቋማት አሸነፉ።
በስዊድናዊ የኬሚስትሪ ባለሙያ አልፍሬድ ኖቤል የተመሰረተው የኖቤል ሽልማት በየዓመቱ እንደሚካሄድ ይታወሳል።
ሽልማቱ በህክምና ፣ ስነጽሁፍ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ሰላም እና ብሌሎች ሙያዎች የተሻለ እና አዲስ አበርክቶ ያላቸውን ሰዎችን ትኩረት ያደርጋል።
በሰላም ዘርፍም የዘንድሮውን ሽልማት የሩሲያ፣ ቤላሩስ ግለሰቦች እንዲሁም የዩክሬን አንድ ተቋም እንዳሸነፉ ሸላሚው አካል የኖቤል ሽልማት ኢንስቲትዩት በድረገጹ አስታውቋል።
የቤላሩሱ አሊስ ቢያንሊያጽኪ እና የሩሲያ እና ዩክሬን ሁለት የሰብዓዊ መብት ተቋማት አሸንፈዋል የተባለ ሲሆን ተሸላሚዎቹ በዩክሬን እና ሩሲያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመሰነድ እና ዓለም እንዲያውቃቸው አድርገዋል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በፈረንጆቹ 2019 ላይ ከ20 ዓመት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነትን አስቀርተውል በሚል የሰላም ኖቤል ሽልማትን ማሸነፋቸው ይታወሳል።
እንዲሁም በ2021 ደግሞ የሩሲያው ጋዜጠኛ ድሚትሪ ሙራቶቭ እና የፊሊፒንሷ ማሪያ ሪሳ በጋራ ሲያሸንፉ በ2020 ደግሞ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሰላም ኖቤል ሽልማቶችን ወስደዋል።