ኖኪያ ከ60 አመት በላይ የተጠቀመበትን አርማ ሊቀይር ነው
ሰማያዊ ቀለም የነበረው የቀድሞው አርማ አምስት የተለያየ ቅርፅ ባላቸውና ሲገጣጠሙ ኖኪያን በሚፈጥሩ ቃላት ተተክቷል
ታሪካዊው የሞባይል ስልክ አምራች አሁን ላይ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ለሌሎች ተቋማት ማቅረብ ላይ አተኩሯል
ታዋቂው የሞባይል ስልክ አምራች ኖኪያ ከ60 አመት በላይ የተገለገለበትን አርማ ሊቀይር መሆኑን አስታወቀ።
በሰማያዊ መደብ ላይ በነጭ ባሰፈረው ሰሙ አለምን ያዳረሰው ኖኪያ፥ አሁን ላይ ዘመኑን የዋጀ አርማ አዘጋጅቻለሁ ብሏል።
አዲሱ አርማ ኖኪያ የሚለውን ቃል የሚፈጥሩ አምስት የተለያየ ቅርፅ ያላቸው ፊደላት የያዘ ነው ብለዋል የኖኪያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፔካ ሉንድማርክ።
የአርማ ለውጡ ያስፈለገውም ኖኪያን አሁንም ድረስ ሞባይል አምራች አድርጎ የመቁጠር ዝንባሌ ስለሚታይ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኖኪያ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ምርቶችን ለስማርት ስልክ አምራቾችና ለቴሌኮሙዩኒኬሽን ተቋማት በማቅረብ ላይ የሚገኝ የቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው።
ኩባንያው በተለይ በ5ጂ ኔትወርክ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ዋና ስራ አስፈፃሚው ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ኖኪያ እንደ ፈር ቀዳጅነቱ ባይሆንም ከስማርት ስልክ ገበያውም አልወጣም።
ለሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚያቀርባቸው ግብአቶች ግን ከአመት አመት እየጨመሩ መሄዳቸው ተነግሯል።
ኖኪያ ባለፈው አመት እንኳን ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ግብአቶችን ለመሰል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አቅርቧል።
በህንድ ከሚገኘው ፋብሪካው ወደ አሜሪካ የሚልከው የስማርት ስልክ ቁጥርም በ2022 በ10 በመቶ ማደጉን ነው ዘገባው የሚያሳየው።
በፈረንጆቹ 1865 በፊንላንድ የተመሰረተው ኖኪያ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ ያለው ተቋም ነው።