ሳምሰንግ S23 ስማርት ስልክ ምን አዳዲስ ገጽታዎች አሉት?
ሶስት ጥራታቸው ከፍ ያለ የኋላ ካሜራዎች ያሉት S23፥ ከአንድ ቀን በላይ ሊያስጠቅም የሚችል ባትሪ ይኖረዋል ተብሏል
በሶስት አማራጮች ለገበያ የሚቀርበው S23 ስማርት ስልክ የሳምሰንግን የተቀዛቀዘ ገበያ እንደሚያንሰራራው ተገምቷል
የደቡብ ኮሪያው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሳምሰንግ ከነገ በስቲያ በይፋ አስተዋውቆ ለገበያ የሚያቀርበው S23 ስማርት ስልክ በብዙዎች እየተጠበቀ ነው።
ከአፕል በመቀጠል የአለማችን ሁለተኛው ስማርት ስልክ ሻጭ ሳምሰንግ በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ነው ስማርት ስልኩን የሚያስተዋውቀው።
S23 ስማርት ስልክ በ2022 የመጨረሻ ሩብ አመት 58 ነጥብ 2 ሚሊየን ስማርት ስልኮችን ለገበያ በማቅረብ ሁለተኛውን ደረጃ የያዘውን ሳምሰንግ የገበያ ድርሻው ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ሳምሰንግ የS23 ስማርት ስልኮችን በሶስት አማራጭ ለገበያ እንደሚያቀርብ የእንግሊዙ ጋዜጣ ኤቭኒንግ ስታንዳርድ ዘግቧል።
S23፣ S23 Plus እና S23 Ultra ስማርት ስልኮች ከS22 ስማርት ስልኮች ምን ይለያቸዋል?
እጅግ ፈጣን እና ጥራት ያላቸው ምስሎችን ማንሳት እንዲችል ስናፕድራገን 8 ጄነሬሽን 2 የተሰኘ ቺፕ ተገጥሞለታል።
ይህም ዘመኑን የዋጀ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን መጠቀም የሚያስችልና እጅግ ፈጣን ግልጋሎትን እንዲሰጥ ያደርገዋል ነው የተባለው።
የ S23 ስማርት ስልክ ስክሪኖችም ወድቀው እንዳይከሰከሱ ኮርኒንግ ጎሬላ ግላስ ከተሰኘ ጠንካራ ቁስ መሰራታቸው ተነግሯል።
የ S23 እና S23 ፕላስ ስማርት ስልኮች የ6 ነጥብ 1 እና 6 ነጥብ 6 ኢንች ስክሪን ስፋት አላቸው።
S23 አልትራም 6 ነጥብ 8 ኢንች ስፋት ያለው ሲሆን፥ ሶስት የኋላ ካሜራዎች አሉት።
ዋናው ካሜራ 200 ሜጋ ፒክስል ጥራት ያለው ምስልን ማስንሳት ያስችላል። የፊት ካሜራውም 40 ሜጋ ፒክስል እና ሴንሰር ተገጥሞለታል።
የካሜራዎቹ ምስልን የማቅረብ አቅም በ10 እጥፍ መጨመሩን ነው እየወጡ ያሉ መረጃዎች የሚያሳዩት።
በS22 ስልኮች ላይ ተገጥሞ የነበረው 108 ሜጋፒክስል ሴንሰር ወደ 200 ሜጋፒክስል ማደጉ በምሽት የሚወሰዱ ምስሎችን ጥራት እጅግ ከፍ ያለ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች።
ሳምሰንግ የአዳዲሶቹ S23 ስልኮቹ የባትሪ ቆይታ ጊዜውን ለማሳደግም ጥረት ማድረጉ ተነግሯል።
ሳምሰንግ ካለፈው አመት S22 ስማርት ስልኮች ባትሪዎች 5 በመቶ የተሻለ የቆይታ ጊዜ ያላቸውን ባትሪዎች በስልኮቹ ላይ ገጥሟል።
ስማርት ስልኮቹ ከ3 ሺህ 900 እስከ 5 ሺህ ሚሊአምፒር አወር አቅም ያላቸው ሲሆን፥ S23 አልትራ ከአንድ ቀን ተኩል በላይ መቆየት የሚችል ባትሪ ተገጥሞለታል ነው የተባለው።
ሳምሰንግ የS23 ስማርት ስልኮችን ለገበያ የሚያቀርብበት ዋጋ እስካሁን ይፋ ባይደረግም በእንግሊዝ ከ950 እስከ 1 ሺህ 500 የአሜሪካ ዶላር ሊያወጡ እንደሚችሉ ኤቭኒንግ ስታንዳርድ አስነብቧል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ ሀገራት ዋጋው ልዩነት እንደሚኖረው ነው የሚገመተው።