በ2022 የስማርት ስልክ ገበያው የደራለት ኩባንያ የትኛው ነው?
በአለም አቀፍ ደረጃ የስማርት ስልክ ገበያው እየተቀዛቀዘ ቢመጣም የአሜሪካው አፕል ኩባንያ በ2022 የመጨረሻ ሩብ አመት ከፍተኛ ሽያጭ ፈጽሟል
በ2022 አዳዲስ ስማርት ስልኮችን ያላስተዋወቀው ሳምሰንግ ደግሞ ይከተላል
በ2022 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ስማርት ስልኮች ለአለም ገበያ ቀርበዋል።
ይህም ከ2013 ወዲህ ዝቅተኛው መሆኑን የገበያ ጥናቶችን የሚያከናውነው አይ ዲ ሲ የተሰኘ ተቋም ይፋ አድርጓል።
ከቻይና ወደ አለም ገበያ የቀረበውም እንዲሁ ከ10 አመት ወዲህ ዝቅተኛው ስለመሆኑ ነው የተነገረው።
ቤጂንግ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት 286 ሚሊየን ስማርት ስልኮችን ለአለም ገበያ ማቅረቧን ጥናቱ አመላክቷል።
ይህም በፈረንጆቹ 2013 ለገበያ ከቀረበው በ13 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ነው ተብሏል።
ከቻይና ምርቶቹን በመጫን ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው የአንድሮይድ ስልክ አምራቹ ቪቮ ሲሆን፥ ከአጠቃላይ ገበያው የ18 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ አለው።
አቅርቦቱን በ34 ያሳደገው ኦነር የተሰኘው ብራንድ ደግሞ ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል።
አፕል በበኩሉ ከቻይና ለአለም ገበያ የስማርት ስልኮቹን በማቅረብ ሶስተኛውን ደረጃ መያዙን ሬውተርስ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ በአለም አቀፍ ደረጃ በ2022 ሽያጩ ከደራላቸው የስማርት ስልክ አምራቾች አፕል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
የአሜሪካው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በ2022 የመጨረሻ ሩብ አመት 72 ነጥ 3 ሚሊየን አይፎን ስልኮችን ለገበያ አቅርቧል።
ይህም ከገበያው የ24 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው ቢያደርግም ከባለፈው አመት በ14 በመቶ ዝቅ ያለ ነው ተብሏል።
ለዚህም በቻይና ካሉ ማምረቻዎቹ ጋር በተያያዘ የገጠመው ችግር እንደምክንያትነት ተጠቅሷል።
የአፕል ኩባንያ በ2022 የመጨረሻ ሩብ አመት ያሳየው አፈጻጸም ከፊት ቢያስቀምጠውም አመታዊ ምርታማነቱ ግን በ4 ነጥብ 4 በመቶ መውረዱ ነው የተጠቆመው።
የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ በበኩሉ 58 ነጥብ 2 ሚሊየን ስማርት ስልኮችን ለገበያ በማቅረብ ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል።
የሳምሰንግም የምርት አቅርቦት ከ15 ነጥብ 6 በመቶ በላይ ቅናሽ ያሳየ ነው ይላል የሲ ኤን ቢ ሲ ዘገባ።
ሳምሰንግ በ2022 አዳዲስ ስማርት ስልኮችን በስፋት አለማስተዋወቁ ለገበያው ድርሻ መቀነስ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ተጠቅሷል።
በ2022 አራተኛው ሩብ አመት የቻይናው ሻውሚ (Xiaomi) 33 ነጥብ 2 ሚሊየን ስማርት ስልኮችን ለአለም ገበያ በማቅረብ ሶስተኛ ደረጃን መያዙም ተነግሯል።
ሻውሚ ለገበያ ያቀረበው ምርት ከ2021 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ26 ነጥብ 3 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ዘገባው አክሏል።
በአጠቃላይ አፕል፣ ሳምሰንግ፣ ሻውሚም ሆነ ሌሎች የቻይና ስማርት ስልክ አምራቾች (ቪቮ፣ ኦፖ) ለገበያ ያቀረቡት ስማርት ስልክ ቅናሽ አሳይቷል።
ለዚህም የኮሮና ወረርሽኝ ይዞት የመጣው የኑሮ ውድነትና ያስከተለው የፍላጎት ማነስ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ነው የተባለው።