በኡጋንዳ እየተካሄደ ያለው የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ጉባኤ ምንድን ነው?
ከ60 ዓመት በፊት የተቋቋመው ይህ ተቋም ከተመድ ቀጥሎ አንጋፋ ዓለም መድረክ ነው
የኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም ሀገራት በዚህ ዓመታዊ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ካምፓላ አቅንተዋል
በኡጋንዳ እየተካሄደ ያለው የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ጉባኤ ምንድን ነው?
የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ወይም በምህጻረ ቃሉ ናም በመባል የሚታወቀው ይህ ተቋም በፈረንጆቹ 1961 ላይ የተቋቋመ ሲሆን ዓለምን ከቀዝቃው ጦርነት ድባቴ ማውጣት ደግሞ ለድርጅቱ መመስረት ዋነኛ ምክንያት ነበር፡፡
120 ሀገራትን በአባልነት የያዘው ይህ ንቅናቄ በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚደርሱ ጭቆናዎችን በጋራ መታገል፣ ጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎችን መደገፍ እና የነጻ ሀገር ምስረታን ማበረታታትም ሌላኛው ዓላማውም ነው፡፡
ከመንግስታቱ ድርጅት በመቀጠል በርካታ ሀገራትን በአባልነት የያዘው ይህ ንቅናቄ ዋና መቀመጫውን ምስራቅ አውሮፓዊቷ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ አሁን ደግሞ የሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ አድርጎ ተመስርቷል፡፡
ድርጅቱ እንዲመሰረትም የቀድሞው የዩጎዝላቪያ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቲቶ፣ የሕንዱ ጃዋህራል ኔህሩ፣ የግብጹ ገማል ናስር፣ የጋናው ክዋሜ ንኩሩማህ እና የኢንዶኔዢያው ሱካርኖ ዋና መስራች መሪዎች እና ሀገራት ነበሩ፡፡
በየዓመቱ ጉባኤውን የሚያደርገው ይህ የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ የመጀመሪያውን ጉባኤ በኩባው ፕሬዝደንት ፊደል ካስትሮ አስተባባሪነት በሀቫና አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ውድቅ ካላደረገች መነጋገር እንደማትፈልግ ሶማሊያ ገለጸች
የዘንድሮው 19ኛው ዓመታዊ ጉባኤም ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ በኡጋንዳ ካምፓላ እየተካሄደ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮም የመሪዎች ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) በዚህ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ካምፓላ የገቡ ሲሆን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር መምከራቸውን በኤክስ አካውንታቸው ላይ ጽፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በጉባኤው “ወደብ አልባ ሀገራት የህዝባቸውን ጥቅም እና ሌሎች ጥያቄዎችን መመለስ እንዳልቻሉ እና ኢትዮጵያም የባህር በር ጥያቄዋን በትብብር ለመመለስ ጥረት እያደረገች ነው” ሲሉ ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የ120 ሀገራት መሪዎች እና ተወካዮች ይሳተፋሉ የተባለ ሲሆን በአጠቃላይ ከ4 ሺህ በላይ እንግዶች ካምፓላ እንደገቡ ተገልጿል፡፡
ዓለማችን እያስተናገደችው ያለው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ የጂኦ ፖለቲካ ፍትጊያ፣ ሽብርተኝነት እና ዓለም አቀፍ ትብብሮች ደግሞ የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳዎች ናቸውም ተብሏል፡፡