የኢትዮጵያ አየር ሀይል “su-30” ተዋጊ ጀቶችን መታጠቁን አስታወቀ
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ “የsu-30 ጄትና የስትራቴጂክ ሰው አልባ አውሮፕላን ባለቤት ሆነናል” ብለዋል
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ su-30 ተዋጊ ጀቱን በማብረር የተለያዩ የአየር ላይ ትእይንቶችን አሳይተዋል
የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዘመናዊ የሆነውን የsu-30 ተዋጊ ጀቶችን እና የስትራቴጂክ ሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላኖችን መታጠቁን አስታወቀ።
የsu-30 ተዋጊ ጀቶች እና የስትራቴጂክ ሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) የመጀመሪያ ዙር ርክክብ በዛሬው እለት መከናወኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል
ርክክቡ ላይ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ “በአለማችን ላይ ተመራጭ የሆኑትን የsu-30 እና የስትራቴጂክ ሰው አልባ አውሮፕላን ባለቤት መሆናችን በሀገራችን ላይ ሊቃጡ የሚሞከሩ ጥቃቶችን ለማክሸፍ ወሳኝ ናቸው” ብለዋል።
የ5ኛ ትውልድ አካል የሆኑት ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖችና የስትራቴጂክ ስው አልባ አውሮፕላኖች አየር ሀይሉን የማዘመን አንዱ አካል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ “አንጋፋው የኢትዮጵያ አየር ሀይል በአፍሪካ በውጊያ አቅሙ፣ በጀግንነቱና በትጥቁ የነበረውን ዝና ዘመኑ በሚጠይቀው መልኩ ለማዘመን እየተሰሩት ያሉት ስራዎች ውጤታማ እየሆኑ ነው” ብለዋል።
የኢፌዴሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ “ተቋሙ የተረከባቸው ዘመናዊ የጦር ጀቶች በተመሳሳይ ጊዜ በአየርና በምድር ላይ ያለ የጠላት ታርጌትን ማውደም የሚችል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም “ኢትዮጵያ የተረከበቻቸው ዘመናዊ የስትራቴጂክ ሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) የጠላትን ዒላማ የማይስቱ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ለጠቅላይ ኤታማዦሩ ሹሙና ለእንግዶች አዲሱን su-30 ተዋጊ ጀት በማብረር የተለያዩ የአየር ላይ ትእይንቶችን አሳይተዋል።