በተመድ ስብሰባ ሀገር ነኝ ብላ የተከሰተችው “ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ ካይላሳ”
ገና በምናብ ላይ ያለችው “ዩ ኤስ ኬ” ፥ ለዜጎቼ ሁሉንም ነገር በነጻ አቀርባለሁ እያለች ነዋሪዎቿን በኦንላይን ምዝገባ ጀምራለች
“የሀገሪቱ መስራች” በኢኳዶር ደሴት ገዝቼ “ዩ ኤስ ኬ”ን እውን አድርጋለሁ ካለ 4 ዓመታት ቢቆጠርም በዩቲዩብ መልዕክት ከማስተላለፍ ውጭ በአካል አልታየም
“ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ ካይላሳ” በዓለም ካርታ ላይ አትታይም፤ በጣም አነስተኛ ሀገር ስለሆነች ግን አይደለም፤ የት እንደምትገኝ ስለማይታወቅ እንጂ።
ይህቺን “ሀገር” ወክለናል ያሉ ሰዎች በዚህ ዓመት በመንግስታቱ ድርጅት ስብሰባዎች ሁለት ጊዜ የመታደማቸው ጉዳይም አነጋጋሪ ሆኗል።
በህንዳዊው ኒትያናንዳ ፓራማሺቫም ከአራት ዓመት በፊት እንደምትመሰረት የተነገረላት “ዩ ኤስ ኬ” እስካሁን ሀገር መሆን አልቻለችም።
ፓራማሺቫም በኢኳዶር ነጻ ደሴትን ገዝቼ እመሰርታታለሁ ያላት “ዩ ኤስ ኬ” እስካሁን በምዕናብ እንጂ በእውን የለችም።
የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ኢኳዶርም በ2019 ይሄው ወሬ ሲሰማ ምንም የማውቀው ነገር የለም ማለቷን ኦዲቲ ሴንትራል አስታውሷል።
ባለፉት አራት ዓመታት በአካል ያልታየው ፓራማሺቫም እና ተቀዛቅዞ የነበረው የአዲሷ ሀገር ምስረታ በ2023 በተመድ ስብሰባዎች በተገኙ ተወካዮቿ ዳግም ማንሰራራት ጀምሯል።
ቪጃያፕሪያ ኒታያናዳ የተባለች እንስት ራሷን የ”ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ ካይላሳ” ቋሚ መልዕክተኛ ነኝ ብላ በማስተዋወቅ ስለሰብአዊ መብት እና ዘላቂ ልማት ስታወራ በርካቶች “ዩ ኤስ ኬ” የት አህጉር ናት በሚለው ሃሳብ ተጠምደው ነበር ይላል ዘገባው።
የመንግስታቱ ድርጅት እንዴት በስብሰባው ላይ እንዲታደሙ ፈቀደ የሚለው ጉዳይም መነጋገሪያ ሆኖ የነበረ ቢሆንም፥ ድርጅቱ “ስብሰባው ላይ ማንም መሳተፍ ይችል ነበር፤ በበይነ መረብ የተካሄደ በመሆኑ” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥቷል።
በእውን የሌለችው ሀገር ተወካይ ነን ያሉ አካላት በትልቁ አለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ይህን መሰሉን መልዕክት ለማስተላለፍ እድል ማግኘታቸው ግን ድርጅቱን ከወቀሳ አላተረፈውም።
”ዩ ኤስ ኬ” ምስረታዬ ሲጠናቀቅ ነጻ ምግብ፣ መጠለያ እና የህክምና አገልግሎት አቀርባለሁ ብላለች።
ባልተመሰረተችው ሀገር መኖር የሚፈልጉ ሰዎችን በኦንላይን ምዝገባ መጀመሩን የሚያሳዩ ማስታወቂያዎችም በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሲዘዋወሩ ይታያል።
ባለፈው ጥር ወር ላይም ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ከ”ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ ካይላሳ” ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት ፈርማለች የሚል ዜናን ሲያሰራጩ ልቦለዳዊ ተግባራቸው ለብዙዎች ሳይገለጥ አልቀረም።
የሂንዱ እምነት ተከታዮችን በነጻ ሀገር ማኖር እፈልጋለሁ የሚለው ፓራማሺቫም በዩቲዩብ እና ሌሎች ማህበራዊ ትስስር ገጾቹ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ ውጭ የት እንዳለ አይታወቅም።
የሴቶች መብት ተከራካሪዎች ፓራማሺቫም በአስገድዶ መድፈርና ሌሎች ወንጀሎች የሚፈለግ ነው፤ እስሩን ሳይጨርስ የተሰወረበት ምክንያት ግልጽ አይደለም ይላሉ።