ልጅ ለወለዱ ዜጎቻቸው ጉርሻ ገንዘብ የሚከፍሉ ሀገራት እነማን ናቸው?
የተወሰኑ የዓለማችን ሀገራት ዜጎቻቸው ልጅ ሲወልዱ እስከ 10 ሺህ ዶላር በመስጠት ላይ ናቸው
ሀንጋሪ ወጣቶች ጋብቻ እንዲመሰርቱና ልጆችን እንዲወልዱ እስከ 30 ሺህ ዩሮ ወለድ አልባ ብድር የሚፈቅድ ህግ አላት
በዓለማችን የተወሰኑ ሀገራት በውስን ሀብት ከፍተኛ የውልደት ምጣኔ በማስመዝገብ ህጻናት በረሃብ የሚሞቱትን ያህል የተትረፈረፈ ሀብት ባላቸው ሀገራት ደግሞ የዜጎች የመውለድ ፍላጎት ጠፍቶ ተረካቢ ትውልዳቸው ያሳስባችዋል፡፡
እነዚህ ዝቅተኛ የመውለድ ምጣኔ ያለባቸው ሀገራት ዜጎቻቸው ልጆች እንዲወልዱ ለማበረታታት ሲሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በስጦታ መልክ ይሰጣሉ፡፡
በበለጸጉት ሀገራት እየታየ ያለው የውልደት ምጣኔ ማሽቆልቆልን ለመግታት ሀገራት ለሚወልዱ ወላጆች የገንዘብ ጉርሻ እና ሌሎች ማበረታቻዎችን ተገባራዊ እያደረጉ ነው።
እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና ቻይና ባሉ ሀገራት የሚደረጉት ማበረታቻዎች ራሱ የውልደት ምጣኔውን ሊያነቃቃው አልቻለም ነው የሚባለው።
እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ ከሆነ በርካታ የዓለማችን ሀገራት ዜጎቻቸው ልጆችን እንዲወልዱላቸው እስከ 10 ሺህ ዶላር ጉርሻ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
በዚህ ዘገባ መሰረት 59 በመቶ የብሪታንያ ዜጎች ልጅ የመውለድ ፍላጎት የሌላቸው ሲሆን መንግስታቸው ግን በአንድ ህጻን ከ14 እስከ 3 ሺህ ዩሮ ድረስ ጉርሻ በመስጠት ላይ ነው፡፡
ሌላኛዋ ሀገር ፊንላንድ ደግሞ ልጆችን ለሚወልዱ ዜጎቿ በአንድ ህጻን እስከ 10 ሺህ ዩሮ የምትከፍል ሲሆን በተለይም በህጻናት ድርቅ የተመታችው ለሰትጃረቪ ከተማ ደግሞ ከገንዘብ በተጨማሪ ሌሎች ዘላቂ ማበረታቻዎችን በመስጠት ትታወቃለች፡፡
ሀንጋሪ ደግሞ ወጣቶች ጋብቻ እንዲመሰርቱ እና ልጆችን እንዲወልዱ እስከ 30 ሺህ ዩሮ ወለድ አልባ ብድር የሚፈቅድ ህግ ያላት ሲሆን ሶስት እና ከዛ በላይ ልጆችን የሚወልዱ ዜጎች ደግሞ ምንም አይነት ግብር የመክፈል ግዴታ የለባቸውም፡፡
ሌላኛዋ ሀገር ግሪክ ደግሞ ልጅ ለወለደች እናት 2 ሺህ ዩሮ ጉርሻ የምትከፍል ሲሆን በጣልያን ደግሞ ልጅ ለወለዱ ወላጆች በየወሩ 192 ዩሮ የማበረታቻ ክፍያ ይፈጸማል።
ፈረንሳይ ደግሞ ለወላጆች በየወሩ እስከ 647 ዩሮ የምትከፍል ሲሆን ስፔን ከሶስት ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ህጻናትን ላሏቸው ወላጆች በየወሩ በአንድ ህጻን 100 ዩሮ በመክፈል ትታወቃለች፡፡