ሰሜን ኮሪያ በርካታ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏ ተነገረ
“አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ለሚያካሂዱት የኒዩክሌር ጦርነት ልምምድ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ” ስትልም አስጠንቅቃለች
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ፒዮንግያንግ ጸብ አጫሪነቷን ከቀጠለች በብዙ እጥፍ የጠነከረ አጻፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ገልጻለች
ሰሜን ኮሪያ በርካታ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ደቡብ ኮሪያ አስታወቀች።
ሲንፖ በተባለ ወደብ አካባቢ በተካሄደው የሚሳኤል ማስወንጨፍ ምን ያህል ክሩዝ ሚሳኤሎች እንደተተኮሱ አልተገለጸም።
በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው ሙከራ ዝርዝር ጉዳዮችን የአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የደህንነት ባለሙያዎች እየመረመሩት ነው ተብሏል።
ፒዮንግያንግ ባለፈው ረቡዕ “ፑልዋሳል -3-31” የተሰኘና የኒዩክሌር አረር መሸከም የሚችል ክሩዝ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኬሲኤንኤ “የአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ እያካሄዱት ያለው ልምምድ ከባድ ዋጋ ያስከፍላቸዋል” ብሏል።
ሀገራቱ የሚያካሂዱትን ልምምድ “የኒዩክሌር ጦርነት ዝግጅት” ነው ያለችው ሰሜን ኮሪያ፥ “ለደም አፋሳሹ ጦርነት ዝግጁ ነኝ” ማለቷንም ዘገባው አክሏል።
ጎረቤቷን ደቡብ ኮሪያ ዋነኛ ጠላት አድርጋ የፈረጀችው ፒዮንግያንግ፥ ከሴኡል ጋር የመዋሃድ ውጥን ሰርዛ የሚሳኤል ማስወንጨፍ ሙከራዋን ቀጥላለች።
ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ትብብሯን አጠናክራ በውሃ ውስጥ ጥቃት የሚፈጽሙ ድሮኖችን ጨምሮ አዳዲስ መሳሪያዎችን መሞከሯን መግፋቷም የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን እያባባሰው ነው።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል፥ ሰሜን ኮሪያ ጸብ አጫሪነቷን ከገፋችበት ሴኡል “በብዙ እጥፍ የሚጠነክር አጻፋዊ እርምጃ ትወሰዳለች” ሲሉ ማሳሰባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ፒዮንግያንግ ላለፉት ሁለት አመታት ያለማቋረጥ የገፋችበት የሚሳኤል ሙከራና የኒዩክሌር ልማት አሜሪካና ደቡብ ኮሪያን ማሳሰቡ ባይቀርም ወደ ግልጽ ጦርነት ያመራል ተብሎ እንደማይጠበቅ ተንታኞች ያነሳሉ።