ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እለት በርካታ ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች
ፒዮንግያንግ በጥቂቱ ሰባት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን መተኮሷን የጃፓን የመከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል
ኪም ጆንግ ኡን የሁለቱን ኮሪያዎች መሪዎች ያጨባበጡት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ፍላጎት እንዳላቸው ተነግሯል
አሜሪካ 47ኛ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዋን በምታደርግበት በዛሬው እለት ሰሜን ኮሪያ በርካታ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች።
የጃፓን የመከላከያ ሚኒስትር ጄን ናካታኒ እንደገለጹት ፒዮንግያንግ በጥቂቱ ሰባት አጭር ርቀት የሚምዘገዘጉ ሚሳኤሎችን ተኩሳለች።
ሚሳኢሎቹ በ100 ኪሎሜትር ከፍታ እስከ 400 ኪሎሜትሮች መምዘግዘጋቸውንና በኮሪያ ልሳነ ምድር እና በጃፓን መካከል በሚገኝ ውሃማ ስፍራ መውደቃቸውንም ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት።
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴርም ጎረቤት ሰሜን ኮሪያ የሴኡልን ወታደራዊ ተቋማትና በሀገሪቱ የሚገኘውን የአሜሪካ የጦር ሰፈር ሊይጠቁ የሚችሉ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ገልጿል።
ፒዮንግያንግ የዛሬውን የሚሳኤል ሙከራ ያደረገችው ኪም ጆንግ ኡን አሜሪካ ድረስ ሊምዘገዘግ የሚችል “ሃውሶንግ-19” የተሰኘ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ባስወነጨፈች በቀናት ልዩነት ነው።
በሙከራው የተበሳጩት አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓንም ባለፈው እሁድ ግዙፍ የሶስትዮሽ የአየር ልምምድ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እለት ያደረገችው የሚሳኤል ሙከራ ዋሽንግተን እና አጋሮቿን ለማስጠንቀቅ ያለመ ሊሆን እንደሚችል ሴኡል ገልጻለች።
ፒዮንግያንግ ሰባተኛ የኒዩክሌር ሙከራ ለማድረግና አሜሪካ የሚደርሰውን አህጉርአቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ለማስወንጨፍ መዘጋጀቷን የሚያሳዩ የደህንነት መረጃዎች እንደደረሷትም አመላክታለች።
ተንታኞች በበኩላቸው የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ኒዩክሌርን እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም አዲሱ/ሷ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በፒዮንግያንግ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን እንዲያነሱ ይፈልጋል ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ ምርጫ ዙሪያ በግልጽ አቋሟን ባትገልጽም የሁለቱን ኮሪያዎች መሪዎች ያጨባበጡት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ፍላጎት አላት ተብሏል።
ዴሞክራቷ ካማላ ሃሪስ በምርጫ ቅስቀሳቸው “ለትራምፕ የሚጮሁ እንደ ኪም ጆንግ ኡን አይነት አምባገነን እና ጨካኝ መሪዎችን ድጋፍ አልፈልግም” ማለታቸው ይታወሳል።
ሃሪስ ወደ ዋይትሃውስ ከገቡ ከአሜሪካ የኒዩክሌር ጥቃት ስጋት አለብኝ የምትለው ፒዮንግያንግ እና ዋሽንግተን ግንኙነት ተካሮ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረት ሊባባስ እንደሚችል ይገመታል።